በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች በአግባቡ ስራ ላይ አልዋሉም - ኢዜአ አማርኛ
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች በአግባቡ ስራ ላይ አልዋሉም
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 8/2011 በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚወጡ ህጎችና መመሪያዎች በአግባቡ ስራ ላይ ባለመዋላቸው በግንባታ ሥራ በሚሳተፉ ዜጎች ላይ የሚደርሰው አደጋ እየተባባሰ መምጣቱ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከአዲስ አበባ ከተማ ኮንስትራክሽን ቢሮ ጋር በመተባበር የጤናና የግንባታ ላይ ደህንነት የህዝብ አስተያየት ዳሰሳ ጥናት ዛሬ ለባለድርሻ አካላት አቅርቧል። በአዲስ አበባ ከተማ የካ፣ ቂርቆስና ቦሌ ክፍለ ከተሞች በግንባታ ላይ ባሉ የ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት የዳሰሳ ጥናት ነው። በዳሰሳ ጥናቱ 600 የግንባታ ሰራተኞች፣ አማካሪዎች፣ ሥራ ተቋራጮችና የህንጻ ባለቤቶች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል ተብሏል። በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የህዝብ አስተያየት ጥናት ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ዳግም መርሻ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ በግንባታ ሥራ ወቅት የሚደርሱ አደጋዎች ለመቀነስ ህጎች ቢወጡም መቀነስ አልተቻለም። በኢትዮጵያ ከ 850 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለውን የግንባታ ዘርፍ ማዘመን የሚያስችሉ ህጎች ቢዘጋጁም የአደጋውን መጠን መቀነስ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የህንፃ አዋጁን ጨምሮ በተለያዩ ህጎች ላይ የሰፈሩት አሰራሮች በአግባቡ ስራ ላይ አለመዋላቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱ ተጠኝዎች 59 ነጥብ 33 በመቶው የግንባታ ሥራ ህጎች በቂ እንደሆኑ፣ 65 ነጥብ 2 በመቶዎቹ ደግሞ ህጎቹ በአግባቡ እንደማይተገበሩ አረጋግጠዋል ብለዋል። አሁን ባለው ህግ አንዳንድ መስተካከል የሚገባቸው አሰራሮች ቢኖሩን በአግባቡ መተግበር ከተቻለ በዘርፉ የሚከሰተውን አደጋ መቀነስ ይቻላል ብለዋል። የሰራተኞች የደህንነት አልባሳት የጥራች ችግር ቢኖርባቸውም ያለውን እየተጠቀሙ ጉዳት እንዲቀንሱ ማስተማርና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በዳሰሳ ጥናቱ 63 ነጥብ 24 በመቶ ጉዳት የሚደርሰው በመወጣጫዎች መሰበር ምክንያት እንደሆነ የዳሰሳ ጥናቱ ማሳየቱን ገልጸዋል። ሰራተኞች፣ አማካሪዎች፣ ሥራ ተቋራጮችና ባለሃብቶች ሁሉም በግንባታ ሥራ የሚደርሰው አደጋ መንስኤዎች በመሆናቸው በቅንጅት መስራትን እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል። ለደህንነት መጠበቂያ ወጪ በውል ስምምነቱ በበቂ ሁኔታ አለመካተት፣ የደህንነት ፖሊሲ እቅድ አለመኖር፣ የሰራተኞች ግዴለሽነትና ሌሎችም ችግሮች አደጋውን ስለሚያባብሱ የጋራ ርብርብን ይጠይቃል ብለዋል። በግንባታ ዘርፉ የመረጃ አሰባሰብና የሪፖርት ሥርዓት ደካማ በመሆኑ በየዓመቱ ምን ያህል ሰዎች ሞቱ ምን ያህሉ ተጎዱ የሚለውን መረጃ እንኳን ማግኘት አዳጋች እንደነበር ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ ተወካይ ኢንጂነር ደመላሽ ከበደ በኮንስትራክሽን አደጋ ላይ የተሰሩ ዘገባዎችን በማሰባሰብና መጠነኛ ዳሰሳ በማካሄድ አደጋውን የሚያሳይ መረጃ መሰባሰቡን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በተዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት መሰረት ዝርዝር መረጃዎች በመለየት የህግ ማዕቀፍ ይዘጋጃል ብለዋል። የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ከህዝብ ዳሰሳ ጥናት ውጤቱ በመነሳት ያዘጋጃቸው የግንባታ ሥራ ቦታዎች ጤንነትና ደህንነት ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቷል። ከግንባታ ዘርፉ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ ባለቤቶች፣ ሰራተኞችና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ሲጸድቅ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።