የኢትዮጵያና የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ተፈራረሙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ነሐሴ 8/2011 የኢትዮጵያና የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተወሳሰበ የመጣውን ሽብርተኝነት በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል እንዳሉት፤ አልሸባብ፣ አልቃይዳና አይ ኤስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል በተለያዩ ወቅቶች ሙከራ አድርገዋል። ነገር ግን የአገሪቱ የጸጥታ ሃይል ተደራጅተው በነበሩ ሽብርተኞች ላይ ስኬታማ እርምጃ በመውሰድ ከአገሪቱ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገልጸዋል። ኢትዮያጵያ ሽብርተኝነትን በብቃት ለመከላከል ከሌሎች አገሮች ጋር ለመሥራት ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰው፤ በተለይ ጠንካራ አጋር ከሆነችው አሜሪካ ጋር ሽብርተኝነትን በዓለም አቀፍና በቀጣናው ደረጃ ለመከላከል ስምምነት ላይ በመድረሷ የፀረ-ሽብር እንቅስቃሴውን ውጤታማ እንደሚያደርገው አመልክተዋል። የአሜሪካ የፌዴራልየምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ረዳት ዳይሬክተር እና የሽብርተኝነት ማጣሪያ ማዕከል ዳይሬክተር ቻርለስ ኬብል በበኩላቸው በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ የደህንነት ተቋማት ሽብርተኞችን በተመለከተ ቴክኒካዊ መረጃዎችን እንደሚለዋወጡ ገልጸዋል። የመረጃ መለዋወጡ ኢትዮጵያና አሜሪካ ለሽብር ጥቃት የመጋለጥ ዕድላቸውን እንደሚቀንሰውና ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ስምምነቱ ሁለቱ አገሮች በአልሸባብ፣ በአልቃይዳና በአይ ኤስ አማካኝነት በአፍሪካ ቀንድ የሚደቅኑትን የሽብር ስጋቶችን በመተንተንና በመተንበይ በሽብር ጥቃት የተነሳ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድሞ የመከላከል እርምጃ እንዲወሰዱ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል። ስምምነቱ በተለይም ደግሞ የአፍሪካ መዲና እና የአለም አቀፍ ተቋማት የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባን እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጓዦች የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሽብር ጥቃት ነጻ እንዲሆኑ ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት የደረሱት ስምምነት ለሁለቱ አገሮች ፋይዳው ከፍተኛ ከመሆኑም ባለፈ በጸረ ሽብር እንቅስቃሴ የጀመሩትን ትብብር ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል፡፡ በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት የሁለቱ አገሮች የደህንነት ተቋማት ሽብርተኞች በስውር ከአገር አገር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መቆጣጠር የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ልውውጥ ያደርጋሉ፡፡ በዚሁ መሰረትም በዛሬው እለት የሁለቱ አገራት የቴክኒክ ቡድን በጋራ ስራ መጀመሩን ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡