በሴት ልጆች ላይ የሚጫኑ ልማዶችን የሚደግፉ መሰረቶችን መቀየር ይገባል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ - ኢዜአ አማርኛ
በሴት ልጆች ላይ የሚጫኑ ልማዶችን የሚደግፉ መሰረቶችን መቀየር ይገባል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ
ኢዜአ ነሐሴ 8 ቀን 2011 ሴት ልጆች በራሳቸው ጉዳይ መወሰን በማይችሉበት ዕድሜ የሚጫኑባቸውን ልማዶች ደግፈው የያዙ ባህላዊና ማኅበራዊ መሰረቶች መቀየር እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሴት ልጆች በራሳቸው ጉዳይ መወሰን በማይችሉበት የዕድሜ ክልልና ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚጫኑባቸው ልማዶች ናቸው። እነዚህን ልማዶች ለመቀየር በኅብረተሰቡ ዘንድ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ተከታታይና ዘላቂ ስራ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። “ልጆቻችን በግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻ ልጅነታቸውን ማጣት የለባቸውም” ያሉት ፕሬዚዳንቷ የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቆም የተዘጋጀውን ብሔራዊ ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርገዋል። ፍኖተ ካርታው መንግስት እ.አ.አ በ2014 በለንደን በተካሄደው ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች ጉባዔ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በ2025 ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም በገባው ቃል መሰረት የተዘጋጀ ነው። በፍኖተ ካርታው ትግበራ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ስልቶች ሴቶችን ማብቃት የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል። ለማኅበረሰብ ንቅናቄ ትኩረት መስጠት፤ ምቹ ተገቢና ጥራት ያለው አገልግሎት፤ የተሻሻለ ህግና የፖሊሲ አፈጻጸም እንዲሁም የመረጃና የሪፖርት አሰጣጥ ስርዓት ዝርጋታ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል። ፍኖተ ካርታው በአምስት ዓመት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል። ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ሙሉ ለሙሉ ከአገሪቷ ለማስወገድ የችግሩን ገጽታ፣ ስርጭትና አዝማሚያ፣ መንስኤና ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ እንዲሁም የሚጠበቁ ውጤቶችን ማሳየት እንዲያስችል ሆኖ ተዘጋጅቷልም ተብሏል። በፌዴራልና በሁሉም ክልሎች የሚከወኑ ተግባራትን ማዕከል በማድረግ ድርጊቱ በሚፈጸምባቸው ወረዳዎች የተለየ ትኩረት ያደረገና በአገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ሊተገበሩ የሚችሉ አዳዲስ የአሰራር ዘዴዎች ተደራጅተው የቀረቡበት እንደሆነም ተጠቁሟል። ፍኖተ ካርታው በሴቶች ህጻትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት ይፋ በሆነበት መርሃ ግብር ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል። እ.አ.አ 2016 በተካሄደ የኢትዮጵያ የስነ-ህዝብና ጤና ጥናት ከ15-49 የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ሴቶች 65 በመቶዎቹ ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል። ከ20-49 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙትም 17 ነጥብ 5 በመቶዎቹ 18 ዓመት ሳይሆናቸው ጋብቻ የፈጸሙ እንደሆኑ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ጸጋዬ ተናግረዋል።