ኢትዮጵያና ኬኒያ ዘርፈ ብዙ ግንኙነታቸውን ማሳደግ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መከሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኬኒያ ዘርፈ ብዙ ግንኙነታቸውን ማሳደግ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2011 በኬኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም በቱርካና የቱሪዝምና የባህል ፌስቲቫል ላይ በመገኘት ከአካባቢው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአገሮቹ መካከል ባለው ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል። በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት አምባሳደር መለስ ዓለም ከዝግጅቱ ጎን ለጎን የሰሜን ኬኒያ ሸለቆ የኢኮኖሚ ቀጠና ዳይሬክተር ጆሴፍ ካሊላፕን አነጋግረዋል። አምባሳደሩ በወቅቱ በአገሮቹ መካከል ያለውን የቱሪዝም፣ድንበር ዘለል ንግድና የአየር ጸባይ ለውጥን መከላከል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከዳይሬክተሩ ጋር መነጋገራቸውን በኬኒያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ የሚገኙት ማህበረሰቦች ይህንኑ ጥረት ተግባራዊ ለማድረግ መስራት ባለባቸው ጉዳይም ላይ መክረዋል። አምባሳደር መለስ ዓለም ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት በተጎራባች ህዝቦች መካከል በባህል ዲፕሎማሲ አማካኝነት የሚፈጠረው መቀራረብ ግጭትን ለማስቀረት እና ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። የኢኮኖሚ ቀጠናው የኬኒያ ሰባት ከተሞችን ዩሲን ጋሹ፣ ትራንስ ንዞዪ፣ ናንዲ፣ ኢልጊዮ ማካዌት፣ ደቡብ ፖኮት፣ ባሪንጎ፣ ሳምቡሩና ቱርካናን የያዘ ነው። የዘንድሮው የቱርካና የባህል እና ቱሪዝም ፌስቲቫል ለ5ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን 10 ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች የየማህበረሰባቸውን ባህል ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።