መምህራኑ ከቻይና የሚቀስሙትን ዕውቀት በአገራቸው ለመተግበር ተዘጋጅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
መምህራኑ ከቻይና የሚቀስሙትን ዕውቀት በአገራቸው ለመተግበር ተዘጋጅተዋል
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 8/2011 የሚቀስሙትን ዕውቀትና ልምድ በአገራቸው ለመተግበር ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን በቻይና ነጻ የትምህርት ዕድል ያገኙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ። የቻይና መንግስት ለሰጠው የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ነፃ የትምህርት ዕድል ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረጡ 31 መምህራን ትናንት አዲስ አበባ ላይ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ መምህራን የሚያገኙትን ዕውቀትና ልምድ በአገራቸው በመተግበር የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል። በቻይና ቆይታቸው ከትምህርታቸው ባሻገር የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን የአገራቸውን መልካም ስም የሚያስጠራ የገጽታ ግንባታ ስራ እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት። በዚህም የኢትዮጵያና የቻይናን ወዳጅነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የማጠናከር ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል። በደን ሳይንስ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ቻይና የሚያቀናው የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር ወርቁ በላይሁን እንዳለው ቻይና የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ከተሞችን አረንጓዴ ማድረግ ላይ አተኩራ እየሰራች ነው። እርሱም በደን ሳይንስ ዘርፍ የቻይናን ልምድና ዕውቀት በመቅሰም አገሩ ላይ ለመተግበር ራዕይ ሰንቋል። በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት እየተካሄደ ላለው አገራዊ ንቅናቄ "የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ትምህርቱ እንደሚያግዘኝ አምናለሁ" ሲልም ተናግሯል። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲው መምህር ዘላለም ክብረት ደግሞ በማቴሪያል ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ትምህርቱ በዘመናዊ መሳሪያዎችና ግብዓቶች ተደግፎ 'እየተሰጠ አይደለም' ይላል። በቻይና በዘርፉ በቴክኖሎጂና በተግባር በተደገፈ ስልጠና የሶስተኛ ዲግሪውን ለመከታተል ዕድል ማግኘቱ በዘርፉ የዳበረ ዕውቀትና ልምድ እንዲኖረው እንደሚያስችለው ገልጿል። ከትምህርቱ የሚያገኘውን ዕውቀትና ቴክኖሎጂ ወደ አገሩ ተመልሶ ለተማሪዎቹ ለማሸጋገር በትጋት እንደሚሰራም ነው የተናገረው። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህሯ አብዮት አብደላም በስፖርት ሳይንስ የሶስተኛ ዲግሪዋን ለመከታተል የትምህርት ዕድል አግኝታለች። "ትምህርቴን አጠናቅቄ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ የቀሰምኩትን ዕውቀት በአገሬ ለመተግበር አቅጃለሁ" ብላለች። በቻይና በሚኖራት ቆይታ የአገሯን ታሪክና ባህል የሚያስተዋውቁ ስራዎች ለማከናወን ማቀዷንም አክላለች። ቻይና በተለይ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ በየዓመቱ ለ10 ሺህ አፍሪካዊያን ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት ላይ ትገኛለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም በየዓመቱ ከ400 በላይ ኢትዮጵያዊያን የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ። በአሁኑ ወቅት 600 ያህል ኢትዮጵያዊያን በቻይና የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያሳያል።