ባዮቴክኖሎጂ-እምቅ የሀብት ምንጭ..‼

214
ወንድማገኝ ሲሳይ (ኢዜአ) “ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ፍኖተ ካርታ ሰነድ ” እንደሚያመለክተው “ባዮቴክኖሎጂ’’ ማለት ሥነ ሕይወታዊ መዋቅሮችንና የተለያዩ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ትስሥራቸውን፣ አንድነትና ልዩነታቸውን በመመርመር፣ ለቴክኖሎጂው የሚያስፈልገውን የዘረመል መዋቅር በመተንተን የብዝሃ ህይወትን ተለያይነትና ልዩ ተፈጥሮ፣ምርታማነትና ጥራትን በመፈተሽ ውጤቶቻቸውን ለሚፈለገው ተግባር ወይም ጠቀሜታ ለማዋል የሚያስችል የዘመኑ ፊት ቀደም (frontier) ሳይንስ ነው። እንደ ሰነዱ ከሆነ በዓለማችን ላይ ባዮቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና ምርታቸውን እጅግ በከፍተኛ መጠን ያሳደጉ ሀገራት በርካቶች ናቸው ። የህክምና መፍትሄ አጥተው ለቆዩ ብዙ የበሽታ አይነቶች ፍቱን መድኃኒቶችን መሥራት ያስቻለም ቴክኖሎጂ  ነው። የግብርና፣ ጤናና አካባቢ የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ለየዘርፉ ኢንዱስትሪ እድገት፣ ምርታማነትና ውጤታማነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ግብዓቶችን በማስገኘትና  ምርትን በብዛትና በጥራት ማሳደግ አስቸሏል። እንዲሁም የሰዎች የመኖሪያና የሥራ አካባቢ ደህንነት አደጋ ላይ ሳይወድቅ የሥነምህዳር እና የሰው ልጆች ጤነኛ መስተጋብር ቀጣይነት ኖሮት እንዲጓዝ ለማድረግ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ሳይንስ ነው። ለዚህም ነው የዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂን እምቅ የሀብት ምንጭነት አስቀድመው የተገነዘቡና በልማት የገሰገሱ ሀገራት ለባዮቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሰው ዛሬ መስኩን በርቀት እየመሩና ትሩፋቱን እየወሰዱ የሚገኙት። ጥቂት ዘግይተው ወደዚህ ቴክኖሎጂ ውስጥ የገቡት እንደ ኪዩባ፣ ኮሪያ፣ ቻይናና ብራዚል ያሉ ሀገራት ባዮቴክኖሎጂን ገንብተው ጥቅሙን መጋራት መጀመራቸው የዚህን ዘርፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማየት የሚረዳ አንድ ናሙና ነው። በዚህ ረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመስኩ እጅግ ወደኋላ የቀረች ቢሆንም የዚህን ቴክኖሎጂ ሂደት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመተንተን ወደ ቴክኖሎጂው ትግበራ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሯን  ነው የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያስታወቀው። ኢንስቲትዩቱ የዚህ እንቅስቃሴ አካል የሆነ ”የመጀመሪያው ብሔራዊ የማቴሪያል ሣይንስና ናኖ ቴክኖሎጂ አውደ ጥናት” ከአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር  በቅርቡ አካሂዷል። በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ካቀረቡት ምሁሯን መካከል የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አማረ ቢኖር አንዱ ናቸው። ዶክተሩ በባዮቴክኖሎጂ ስር በሚገኙ  የናኖ ቴክኖሎጂና ማቴሪያል ሣይንስ ጠቅላላ እይታ ረገድ  ከዓለም አቀፍ እስከ  አገራችን ምን እንደሚመስል፣በዓለም ደረጃ እንዴት እያደገ እንዳለ፣በኢትዮጵያ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በቀጣይ እንዴት መሄድ እንዳለብን በጽሁፋቸው ዳስሰዋል። የባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ ዓለማችን እየገጠሟት ላሉ የተለያዩ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለማስገኘትና የሰው ልጅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግሥጋሴ ሳይደነቃቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ መጓዝ እንዲችልም ገና ብዙ ተስፋ የተጣለበት የዘመኑ ሳይንስ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ቴክኖሎጂውን በሰፊው ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ ከሆኑት 27 በላይ የዓለማችን ሀገሮች ውስጥ አሜሪካ ፣ ብራዚልና አርጀንቲና ግንባር ቀደም ናቸው። በአነስተኛ ደረጃ ደግሞ ካናዳ፣ ህንድ ፣ ቻይና ፣ ፓራጓይ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ፓኪስታንና ቡርኪና ፋሶ  የሚገኙበት ሲሆን የሀገራቸውን የእርሻ መሬት በተለያዩ የዘረመል ምህንድስና ምርቶች እንደሸፈኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ናኖ ቴክኖሎጂና ማቴሪያል ሣይንስ ያልታሰበ ነገር የመፍጠር አቅም አላቸው የሚሉት  ዶክተር አማረ  ሳይንሱ የብዙ አገራትን ኢኮኖሚ እያሽከረከረ ይገኛል። በኤሌክትሪካልና ሜካኒካል ባህሪያቸው የምንፈልገውን በርካታ ቴክኖሎጂ በማሻሻል ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማዋል እንደምንችል በመጠቆም። እንደሳቸው ገለፃ የዓለም ኢኮኖሚ፣ የእውቀት ኢኮኖሚ እየሆነ መምጣቱና ባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ የዚህ አካል መሆኑ ሀገሪቷ አቅሟን በጊዜ ገንብታ በነገው ዓለም የተሻለ ተወዳዳሪ ልትሆን ይገባል። ሌላው ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢ  በኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ሴንተር- የናኖ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጋሞ በበኩላቸው  የባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ስርፀትን እንደ መሣሪያ በመውሰድ የሕዝባቸውን ኑሮ የቀየሩና ኢኮኖሚያቸውን ተወዳዳሪ ያደረጉ አገራት ተፈጥረዋል። የባዮቴክኖሎጂ ልማት ለኢትዮጵያ አስፈላጊነቱና ለሀገሪቱ ልማት ሊያበረክት የሚችለው አቅም ከፍተኛ መሆኑ አያጠራርም። ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትራንስፎርሜሽን ባዮቴክኖሎጂ አስተማማኝ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችል መሣሪያ መሆኑን በመረዳትም የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም መደረጉን ነው ያስረዱት። ምንም እንኳን ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ ቢኖረውም በዘጠኝ የምርምር መስኮች ማለትም በባዮቴክኖሎጂ ስር በሚገኙ በጤና፣ በግብርና፣ በአካባቢ፣ በኢንዱስትሪያል፣ በባዮ ኢንፎርማቲክስ፣በናኖ ቴክኖሎጂ፣በምልስ ምህንድስና እና በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ የሚባሉ የትኩረት መስኮችን በመምረጥ እየሰራ መሆኑን በመጠቆም። በነዚህ የቴክኖሎጂ መስክ አቅም መፍጠር ለሀገሪቱ ልማት ቀጣይነትና ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። በሀገሪቱ በፍጥነት እያደገ ያለውን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና በተለይ በስትራቴጂያዊ የምግብ ሰብሎችና እንስሳት ሀብት ምርቶች ራስን ከመቻል አልፎ በተትረፈረፈ  ምርት አስተማማኝ ደጀን ለመፍጠር አቅም ይፈጥራል። ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ፣ ከውጪ የሚገባ ምርትን የሚተኩ፣ ለውጪ ንግድ የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን ምርታማነት በጥራት ለማሳደግና በማቅረብ ረገድ ምርምሩና ስርጸቱ ሰፊ ጥቅም ያስገኛል ይላሉ። ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ከሰጣቸው የምርምር መስኮች ውስጥ በማቴሪያልና ናኖ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተካሄዱ ጥናታዊ ጽሁፎች  በተለይ በህክምናው፣ኢንዱስትሪ፣ለአካባቢና ኢነርጂ ልማት ያላቸውን ሀገራዊ ፋይዳና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካሪኩለም ዝግጅት የሚሆን ግብዓት ለማሰባሰብ ታስቦ አውደ ጥናቱ መዘጋጀቱንም አውስተዋል። የማቴሪያል ሣይንስ ከውጭ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን በራስ አቅም ሀገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል ያሉት ደግሞ በኢንስቲትዩት የኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ሴንተር-የማቴሪያል ሣይንስ ዳይሬክተር ዶክተር ወንድማገኝ ማሞ ናቸው። ኢንስቲትዩቱ የብረትና ሴራመክስ ውጤቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ምርምሮችን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ በማመልከት። ዋና ግቡም በራሳችን አቅም የሚካሄድ የላቀ ሀገራዊ የባዮቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ማረጋገጥ እንደሆነ ነው ዶክተር ወንድማገኝ ያስገነዘቡት። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ እንዳሉት ከኮሪያ ልምድ በመቅሰም የማቴሪያል ሣይንስ የትምህርት መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲው ተከፍቷል። ለትምህርት ዘርፉና ለምርምር ስራው አመቺና ዘመናዊ መሳሪያዎች ተሟልተው በጥቂት የተሻለ አቅም ባላቸው የዲግሪ ተማሪዎች ትምህርቱ መጀመሩን እንዲሁ። በቀጣይ ዩኒቨርስቲው የማቴሪያል ሳይንስ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋምና የዶክተሬት ትምህርት ለማስጀመር የስርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ተሾመ አስታውቀዋል። የሃረማያ ዩኒቨርሰቲ መምህር ዶክተር አቢ ታደሰ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመለከቱትም በዓለም ላይ 67 የመጀመሪያ ድግሪ፣157 የሁለተኛ  ድግሪና 46 ደግሞ የዶክተሬት ድግሪ መርሐ ግብር በማቴሪያል ሣይንስና ናኖ ቴክኖሎጂ ትምህርት ተጀምሯል። ትምህርቱ እየተሰጠ ያለው አሜሪካ፣ዩናትድ ኪንግ ደም፣ቱርክ፣ሲንጋፖርና ህንድን  ጨምሮ በ15 አገራት በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች መሆኑን ጠቅሰዋል። ዶክተር አቢ እንደሚሉት ባዮቴክኖሎጂው ዘላቂነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ የትምህርት መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊስፋፋ ይገባል። አሁን አሁን ዓለማችንን የሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት፣ ከዚህ በፊት ያልታወቁ አዳዲስ የበሽታ አይነቶች መከሰት ተግዳሮት ሆኗል። ወደ ሀገራችን ስንመጣም የኢኮኖሚያችን ዋልታ በሆነው የግብርና ምርቶች በአየር ንብረት ለውጥ፣ድርቅ፣በአሜሪካ መጤ ተምችና በሌሎችም አካባቢያዊ ችግሮች በተደጋጋሚ ሲጎዱም ይታያል። የኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ የኃይል ፍላጎት እየናረ መሄድ፣ የኢንዱስትሪ የምርት ሥርዓቶችም በአካባቢ ላይ እያደረሱ ያለውን ብክለት የመቆጣጠርና ቆሻሻን ወደ ጠቃሚ ቁስነት የመቀየር እድል የዘመናዊ ባዮቴክኖሎጂን ተፈላጊነት በከፍተኛ መጠን እያጎላው ስለሚሄድ ግዙፍ የባዮቴክኖሎጂ አቅምን በሀገራችን መገንባት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም እንላለን…‼።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም