ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢዎች ግጭቶችን ለማስወገድ የባህል ዲፕሎማሲን መጠቀም ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 8/2011   በኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደር ማህበረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስወገድና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ልማት ለማምጣት የባህል ዲፕሎማሲን መጠቀም እንደሚገባ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል። በቱርካና ባህል እና ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ ሎድዋር የሚገኙት በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ከክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት በተጎራባች ህዝቦች መካከል በባህል ዲፕሎማሲ አማካኝነት የሚፈጠረው መቀራረብ ግጭትን ለማስቀረት እና ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ ረገድ የአተከር ወይም የኛቴኬሪን ቋንቋ ተነጋሪ በሆኑት የኛንጋቶም፣ የዳሰነች፣ የቱርካና፣ የቶፖሳ፣የካራሞጆንግ፣ የጂ እና የቴሶ ህዝቦች መድረክ የሆነው የቱርካና የባህል እና ቱሪዝም ፌስቲቫልም በማህበረሰቦቹ መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ከማስቀረት እና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ የመተባበር መንፈስ እንዲኖር የጎላ ሚና ይጫወታል ብለዋል። በዝግጅቱ ላይ ከደቡብ ኢትዮጵያ 40 (አርባ) ያህል ተሳታፊዎች ዝግጅታቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል። ፌስቲቫሉ ማህበረሰቦቹ እንዲተዋወቁ እና እንዲቀራረቡ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እና በጋራ የልማት ጥያቄዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር በማስቻል በመካከላቸው የሚከሰቱ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀንሱ አስችሏል ብለዋል። የቱርካና ክልል ኮሚሽነር ሙታማ ዋምቡአ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ኬንያ ረዥም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው ለተጎራባች ማህበረሰቦች የተፈጠረው ይህ የባህል መድረክ በተለያዩ ሲከሰቱ የቆዩ የቁም ከብት ቅሚያዎች እና ግጭቶች እንደቀንሱ አስችሏል ብለዋል። የዘንድሮው የቱርካና የባህል እና ቱሪዝም ፌስቲቫል ለ5ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን እስከ አስር ሺህ ያህል ተሳታፊዎች የየማህበረሰባቸውን ባህል ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም