የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን 2 ሺህ 500 ችግኞች ተከላ አካሄደች

98
ነሀሴ 7 /2011 የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽን አገልግሎቱን በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ዛሬ የችግኝ ተከላ አካሂዷል። የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ኮሚሽነር አቶ ግርማ ቦረሼ እንደሚሉት፤ የችግኝ ተከላው የተከናወነው በተለያየ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎችን ምሳሌ ለማድረግ በማለም ነው። የቤተ-ክርስቲያኒቱን ፕሬዚዳንት ጨምሮ የተለያዩ ሃላፊዎችና የኮሚሽኑ ሰራተኞች በተሳተፉበት የችግኝ ተከላ ስነ-ስርዓት፤ ጉዲና ቱምሳ የማሰልጠኛ ማዕከልን ጨምሮ በሶስት ቦታዎች ላይ ተከላው ተካሂዷል። ኮሚሽኑ ካሁን ቀደም በክልሎች ጭምር የተለያዩ ስፍራዎች ላይ በችግኝ ተከላ ሰፊ ስራዎች መስራቱን አቶ ግርማ ገልጸዋል። የተተከሉት ችግኞች ለምግብነት፣ የአካባቢ ጥበቃና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ናቸው። ኮሚሽኑ ባሁን ሰዓት ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የእርዳታ ስራዎች እያከናወነ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ከ25 ሺህ በላይ ወላጅ ያጡ ህጻናትን እያስተማረ ይገኛል። ኮሚሽኑ የልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን ነድፎ ወደ ስራ ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም