ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን በችግር ፈቺ ምርምሮች የሚጠበቅባቸውን እየሰሩ አይደለም

ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን በችግር ፈቺ ምርምሮች ረገድ የተሰጣቸው ትኩረት ከማነሱ የተነሳ በሚጠበቅባቸው ልክ እየሰሩ እንዳልሆነ ተገለጸ።
ችግር ፈቺ ምርምሮቹን በተጠናከረ መልኩ እንዲሰራ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑንሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ያስገኙ ሲሆን በዚህም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር 50 መድረሳቸው ይታወቃል።ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ስራ በተጨማሪ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩሩም የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል። ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ በሀገሪቷ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመከተል የልየታ ስራ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እየተሰራ ነው። በሚኒስቴሩ የምርምር፤ ማህበረሰብ አገልግሎት፤ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ተቋማት ትስስር ዳይሬክተር እንዲሁም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን ቢኖር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚሰሩ ምርምሮችና ተግባራቱን በሚያግዙ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ በሀገሪቷ በከፍተኛ ትምህርት ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተገኝተዋል። ተቋማቱ  ከመማር ማስተማሩ ስራ ጋር ሲነጻጸር በሀገራችን ለምርምር የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ በአብዛኛው ችግር ፈቺ ምርምሮች በተጠበቀው መልኩ እንዳይካሄዱ ምክንያት ሆኗል። ለአብነትም ለምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሚመደበው በጀት ከሌሎች ክፍሎች ጋር ሲነጻጸር አናሳ መሆኑ የከፍተኛ ትምርት ተቋማት ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮች ላይ እንዳያተኩሩ ሌላው ምክንያት መሆኑን በመግለፅ። ችግር ፈቺ ምርምሮች ከሰው ኃይል፣ ከገንዘብና ከግብዓት አንፃር ከፍተኛ ሃብት የሚጠይቁ ቢሆኑም በሀገሪቷ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ በምርምር ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎች እንዲሁም ለምርምር የሚውሉ አላቂና ቋሚ ግብዓቶች ውስን ናቸው ይላሉ። በተጨማሪም የመምህራን ቅጥር ስርዓቱ ላይም ክፍተት መኖሩን የገለጹት ዶክተር ሰለሞን፤ ይህም በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲ መምህራን 75 በመቶ በመማር ማስተማር ላይ እንዲያተኩሩ ቀሪዎቹ 25 በመቶዎቹ ብቻ በምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ እንዲያውሉ የሚያደርግ ስርዓት መኖሩ ለችግሩ ተጨማሪ መንስኤ መሆኑን አብራርተዋል። በሌሎች ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን በመማር ማስተማር ላይ ብቻ ሳይሆን በምርምር ማዕከላት አሊያም በልህቀት ማዕከላት ሙሉ ሰዓታቸውን በመጠቀም ምርምር ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስችል የአቀጣጠር ስርዓት እንዳለም ገልፀው በኢትዮጵያ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች እነዲሁም ከሌሎች ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች በስተቀር ይህ ዓይነት አሰራር አለመኖሩም መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል። በግብዓት የተሟሉ ቤተሙከራዎች በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲዎች አለመኖሩንም ዶክተር ሰለሞን በምክንያትነት አንስተዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተቋቋመ ወራትን ያስቆጠረ ቢሆንም የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት ሲባል በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ዶክተር ሰለሞን ተናግረዋል። ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ለማተኮር የተለያዩ ተግባራት እየተሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶክተር ሰለሞን፤ ሚኒስቴሩ የተሻለ አደረጃጀት ፈጥሮ እየሰራ መሆኑን አክለዋል። በሀገሪቷ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በይዘታቸው የአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ አደረጃጀት መስፈርት ያላቸው በመሆኑ አለም አቀፋዊ የዩኒቨርሲቲ አደረጃጀትን በመፈተሸ የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት አተኩረው እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል የዩኒቨርሲቲ ልየታ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል። ያም ሆኖ የሀገሪቷ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ፈች ምርምር ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለባቸው የሚሰነዘር አስተያየት ቢኖርም አለም አቀፋዊ ተሞክሮ የሚያሳየው የመሰረታዊ ምርምር ስራዎችም ለሀገር እድገት የራሳቸው የሆነ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይናገራሉ ዶክረት ሰለሞን። ለመሰረታዊ ምርምር ስራዎች ሙሉ በሙሉ ትኩረት አለመስጠት ተገቢ አለመሆኑን የሚናገሩት ዳይረክተሩ። ለአብነትም በእስራኤልና ደቡብ ኮሪያ ሀገራት የሚገኙ መሰረታዊ የምርምር ተቋማት ያላቸውን ሀገራዊ ጠቀሜታ ያወሳሉ። በኢትዮጵያም በአብዛኛው ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩት መሰረታዊ የምርምር ስራዎች መሆናቸውን በመጠቆም። ለወደፊቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ምርምሮቹ እንዲሰሩ ብቻ ሳይሆን የሚሰሩ ምርምሮችም የተሻለ አገራዊ ጠቀሜታ ማበርከት እንዲችሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የምርምር ስርዓቱን የሚመራና በሳይንስ ማህበረሰቡ የሚመራ ብሄራዊ የምርምር ፋውንዴሽን ሊኖር እንደሚገባም ገልፀዋል። በዚህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር የምርምር ስርዓቱን ከሌሎች ሀገራት ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመነፃፀር መፈተሽ አስፈላጊ መሆኑኑን በመጠቆም። ይህን ተግባር የሚከውን ገለልተኛ የሆኑና ልምድ ባካበቱ ተመራማሪዎች የሚመራ የብሄራዊ ምርምር ካውንስል ወይም ፋውንዴሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ ቢቋቋም የሚል ሃሳብንም ሰንዝረዋል። ካውንስሉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋምና ሀገራዊ የምርምር ተቋማት እንዲሁም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመግለፅ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም