የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል ዛሬ ፍጻሜውን አግኝቷል
አዲስ አበባ ሰኔ 6/2010 በፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች መካከል የሚካሄደው ዓመታዊ 'የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል' ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተጠናቋል። ከግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ፌስቲቫል የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሸን በጋራ አዘጋጅተውታል። በፌስቲቫሉ ላይ በሁለቱም ጾታዎች ከ16 የፌዴራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ 870 ሠራተኞች በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፈውበታል። አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቮሊቦልና ዳርት የስፖርት ዓይነቶች ሠራተኞቹ ከተወዳደሩባቸው መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። 'የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል' የኦሊምፒክና የሲቪል ሰርቪስ ቀንን ታሳቢ በማድረግ የሚካሄድ ነው። በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ መንግስቱ ሳህሌ እንደገለጹት የውድድሩ ዓላማ የስፖርት ፖሊሲውን መሰረት በማድረግ ህብረተሰቡ በሚማርበት፣ በሚሰራበትና በሚኖርበት ቦታ ሁሉ የስፖርቱ ተጠቃሚ ማድረግ ነው። የፌስቲቫሉ መካሄድ በሠራተኛው መካከል የእርስ በርስ ትውውቅን ለማጠናከርና በሥራ ላይ ያለውን ውጤታማነት በማሳደግ ረገድም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳበረከተም ተናግረዋል። ውድድሩ ህብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደው መሰረት ከአነስተኛ ደረጃ በመነሳት የአካል እንቅስቃሴ በማድረግ ጤንነቱን እንዲጠብቅ ለማስገንዘብ የጎላ ሚና እንደነበረውም አመልክተዋል። ከሌሎቹ ዓመታት አንጻር የተሳታፊ መስሪያ ቤቶች ቁጥር መቀነሱንና ይህም የሆነው እንደ ሌሎቹ ዓመታት ስፋት ያለው የቅስቀሳ ስራ በበቂ ሁኔታ አለመሰራቱና በውድድሩ አዘጋጆች መካከል የነበረው የአሰራር ቅንጅት ክፍተት እንደሆነ ነው አቶ መንግስቱ ያስረዱት። በቀጣይ ችግሮቹን በመፍታት ፌስቲቫሉ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የተሳታፊዎች ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራልም ብለዋል። በዘጠኙም የስፖርት ዓይነቶች በነጠላና በቡድን በተካሄዱ ውድድሮች ላሸነፉ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ እንዲሁም በየስፖርቶቹ አጠቃላይ አሸናፊ ለሆኑ መስሪያ ቤቶች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ለአሸናፊዎች የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል። 'የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል' ዛሬ ሲጠናቀቅ ሰርከስና ሌሎች አዝናኝ ውድድሮች በአዲስ አበባ ስታዲየም ለእይታ ቀርበዋል።