ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሩስያው ገጣሚ ፑሽኪን ሁለተኛ የመታሰቢያ ሐውልት በአዲስ አበባ ልትገነባ እንደሆነ ተገለፀ

ኢዜአ ነሃሴ 7/2011 ኢትዮጵያ በመዲናዋ ለታዋቂው ሩሲያዊው ገጣሚ አሌክሳንደር ፑሽኪን ሁለተኛ የመታሰቢያ ሐውልት ልትገነባ ዕቅድ መያዟን በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑን ዋቢ በማድረግ ስፑትኒክ የተሰኘው የሩሲያ ታዋቂ ድረ ገፅ ዘገበ። ፑሽኪን (1799-1837) የወታደራዊ መሃንዲስ እና ጄኔራል የሆነው የአብራሃም ጋኒባል የዘር ሐረግ ሲሆን በ 17 ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በሰሜናዊ አቢሲኒያ ወይም በኢትዮጵያ ግዛት እንደተወለደ መረጃው አስታውሷል። የዘር ሃረጉ አመጣጥ እሰካሁንም አከራካሪ ሆኖ የቆየው ጋኒባል በወቅቱ የኦቶማን ኤምፓይር ተብሎ በሚጠራው ግዛት በባርነት ተግዞ ከሄደ በኋላ ለታላቁ የሩሲያ ንጉስ ፔጥሮስ በስጦታ መልክ እንደተሰጠ መረጃው አስታውሷል። በአዲስ አበባ የሩሲያ የባህል ማዕከል እና በገጣሚው ስም የሚጠራ አደባባይ እንዳለ የተናገሩት አምባሳደር አለማየሁ በቀጣይ አንድ ትልቅ የመታሰቢያ ሐውልት ለመገንባት ዕቅድ እንደተያዘም ለመረጃው ምንጭ ገልፀዋል። አምባሳደሩ አክለውም ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም የኢትዮጵያ የሥነ ሕንፃና የታሪክ ምሁራን ቡድን በፕሮጀክቱ ላይ እየሠራ መሆኑን  ገልፀዋል። አዲስ አበባ ለፑሽኪን በራሱ ስም በተሰየመው አደባባይ አቅራቢያ አንድ ትንሽ የመታሰቢያ ሐውልት እንደገነባች አምባሳደሩ ለድረ ገፁ መናገራቸውንም ዘገባው አንስቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም