ቀጥታ፡

ህብረተሰቡን በሚያስተሳስሩ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 07/2011 መንግስት  መልካም ነገር ይዞ ከተነሳ ማንም ሰው የሃይማኖትም ሆነ የብሄር ልዩነት ሳይገድበው በጋራ እንዲቆም አጋዥ በመሆኑ ህብረተሰቡን በሚያስተሳስሩ ስራዎች ላይ  ማተኮር እንደሚገባ የሃይማኖት  አባቶች ተናገሩ።

የታላቁ አንዋር መስጊድ ኢማም  ሓጂ ጣሃ መሃመድ ሃሩ በሀገሪቱ የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ እና  የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ችግሮችን ለመቅረፍ ሕብረተሰቡን ያለ ልዩነት ማሳተፍ የሚያስችሉ እቅዶችን ነድፎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም እና መፈናቀልን ለማስወገድ የሃይማኖት አባቶች ስለ ፍቅር፣ ሰላም እና አንድነት  ማስተማር  አለባቸውም ነው ያሉት።

“የኢትዮጵያ ህዝብ በውስጡ ምንም ዓይነት ሸር የለውም” ያሉት ሓጂ ጣሃ፤ በሰላም ዙሪያ የሁሉም ሰው እውቀትና ሃሳብ አንድ ባለመሆኑ በቀጣይ ማስተማር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ከግጭት እና ሰላም እጦት ተጠቃሚ እንደሌለ የገለጹት ሓጂ ጣሃ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ህብረተሰቡን እርስ በእርስ የሚያጋጩ አጀንዳዎችን ከማራገብ እንዲቆጠቡም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ወጣቱም ዓላማ ሊኖረው  እንደሚገባ ገልጸው፤ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ስራ አጥ ወጣቶች ወደ ስራ በማሰማራት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በተለያዩ የሃማኖት ተቋምት በየደረጃው ያሉት የእምነት አባቶች ስለ ሰላም ከማስተማር በተጨማሪ በተግባር ራሳቸው የሰላም አርአያ መሆን አለባቸው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ ናቸው፡፡

መንግስትም የህብረተሰቡን አንድነት የሚያጠናክሩና ልዩነቶችን የሚያጠቡ  ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ተናግረዋል።

በልዩነት ላይ ያተኮሩ የታሪክ ትርክቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች መበራከት ለግጭቶች መባባስ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ የተናገሩት ፓስተር ፃዲቁ፤  የችግሩ ምንጭ    ፖለቲከኞችና  አክቲቪስቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመልካም ዓላማ በጋራ የመሰለፍ የዳበረ ልምድ አለው ያሉት ፓስተር ፃዲቁ፤ ለዚህ ማሳያም  በአንድ ቀን  353 ሚሊዮን ችግኝ በላይ የተተከለበትን ሃምሌ 22/2011 ዓ.ም ማሳያ ነው ብሏል፡፡

መንግስት ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ መላውን ህብረተሰብ ከጎኑ በማሳለፍ በአገሪቱ ሰላም የሚሰፍንበት እና  ኢኮኖሚዋ የሚያሳድግበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ሃይሎች  ፍላጎታቸውን  በሃይል በሰው ላይ  ለመጫን  በሚያደርጉት ሙከራ የአገሪቱን ሰላም እያደፈረሰ መሆኑን የተናገሩት ፓስተሩ፤  የፖለቲካ ልዩነቶች የሚያደርሱትን ጉዳት መፍታት የሚቻለው ሰላም ሲኖር  እንደሆነም ተናግረዋል።

መንግስትም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ መመለስ እንዳለበት ገልጸው፤ ህብረተሰቡም ለዓመታት የተከማቹ ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር እንዲመለስለት ከመሻት ይልቅ በትዕግስት መጠበቅ  አለበት ብለዋል።

ሰላምን ለማስፈን በሚካሄድ እንቅስቃሴ ውስጥ  ሕዝቡን በማሳተፍ ከሃይማኖት አባቶች ጋር  በጋር  መስራት ዘላቂ መፍትሄ ነው ያሉት ደግሞ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መምህር ዳንኤል ሰይፌሚካኤል ናቸው፡፡

በተለያዩ አከባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እና የሰላም መደፍረስ ችግር  የሃይማኖት ተቋማት እና የእምነት አባቶች ጭምር ሰለባ እንደሆኑ ተናግረው፤ የሃይማኖት አባቶች ህብረተሰቡ ወደ ሰላም እና ፍቅር እንዲመጣ የማስተማር ግዴታ አለባቸው ብለዋል፡፡

ሰላምን ለማስፈን የሃይማኖት አስተምህሮ ካለውን ከፍተኛ ሚና ጎን ለጎን መንግስትም  ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላም የማስፈን ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በፖለቲካ አስተሳሰብ ያለው ልዩነት ለግጭት መንስኤ ሊሆን አይገባም ያሉት መምህር ዳንኤል፤ ከወቅታዊ ስሜት ይልቅ ዘላቂ ጥቅም በሚያስገኙ ጉዳዮችና ህብረተሰቡን የሚያስተሳስሩ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም