ስፖርቱን ለመለወጥና ለማሻሻል በመዲናዋ የማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ይገባቸዋል -የስፖርት ጋዜጠኞች - ኢዜአ አማርኛ
ስፖርቱን ለመለወጥና ለማሻሻል በመዲናዋ የማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ይገባቸዋል -የስፖርት ጋዜጠኞች
ነሐሴ 06 ቀን 2011 ስፖርቱን ለመለወጥና ለማሻሻል በመዲናዋ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲስፋፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ጠየቁ። የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በዘርፉ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲሁም የቀጣይ ስፖርቱ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ ዛሬ ከስፖርት ጋዜጠኞች ጋር ተወያይቷል። ጋዜጠኞቹ ለስፖርቱ መዳካም በመዲናዋ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጦትና ስፖርቱ በባለሙያዎች አለመመራቱን በዋናነት አንስተዋል። በመዲናዋ ስፖርቱ እንዲስፋፋ በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባትና ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም እንዲሁ። የሸገር ሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኛ አስፋው ስለሺ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በየቦታው እየተጀመሩ ባለመጠናቀቃቸውና ለማስፋፋት እቅድ እየወጣ ተግባራዊነቱ ላይ ውስንነት እንዳለ ተናግሯል። ለዚህም የስፖርቱ አመራር የስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታዎች ላይ ትኩረት በመስጠትና በሙያው ያለፉ አመራሮችን መድበው ሊያሰራ እንደሚገባ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የስፖርት ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመም ስፖርቱ ከስር መሰረቱ እንዲያድግ ከተፈለገ ከህጻናት ጀምረው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሊያድርጉበት የሚችሉበት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሊኖሩ ይገባል ብሏል። በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንዲሁም በትምህርት ቤቶች አካባቢ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ሊመቻቹ እንደሚገባም ተናግሯል። የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የስፖርት ጋዜጠኛ ዮናስ ሞላ በሰጠው አስተያየት ደግሞ የስፖርት አመራሮች በስፖርቱ በቂ እውቀትና ግንዛቤ የሌላቸው በመሆናቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ ሄደዋል፤ ይህ ደግሞ ስፖርቱን ማዳከሙን ይገልጻል። ለዚህም የስፖርት አመራሩ ለማዘውተሪያ ስፍራዎች ቅድሚያ በመስጠትና የስፖርት ባለሙያዎችን ወደ ስፖርቱ ማምጣት ይገባል ብሏል። አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ስፖርቱን ለማሳደግ ከስፖርት ኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አመልክቷል። የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አረጋዊ ስፖርቱን ለማሳደግና ህዝባዊ ለማድረግ ምክክሮችና ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውና የዛሬው ውይይትም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል። ኮሚሽኑ የታዳጊዎችን ስፖርት ማሳደግ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋፋት፣ የማስ ስፖርት እንቅስቃሴን ማጎልበትና ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በተለይም በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ግንባታዎች ላይ እየታየ ያለውን መጓተት ለመፍታት የግንባታዎቹን ስራ ለአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ መስጠቱን አመልክተዋል። የስፖርት ኮሚሽኑ የሚገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ዝርዝር ለአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ በመስጠት ኮንስትራክሽን ቢሮው በግንባታው ላይ ትልቅ ድርሻ እንዲኖረው መደረጉንና ስፖርት ኮሚሽኑም ግንባታዎቹ የደረሱበትን ደረጃ እንደሚከታተልም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ የስፖርቱን እድገት ለማሳካት መገናኛ ብዙሃን ከስፖርት ኮሚሽኑ ጋር አብረው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።