ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከአቻ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመሩትን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከአቻ የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመሩትን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ተጠቆመ
ጎንደር (ኢዜአ) ነሀሴ 6 ቀን 2011ዓ.ም-የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከአቻ የውጪ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጀመሩትን ግንኙነት ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ አሳሰቡ፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጃፓን ከሚገኘው “ቶኩሹማ ዩንቨርሲቲ” ጋር የጀመረውን ግንኙነት ዳግም ማጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ላለፉት 17 ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የጋራ የምርምር አጀንዳዎችን በመቅረጽ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የጃፓኑ ቶኩሹማ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የማህበረሰብ ምርምሮችን በማካሄድ ለጃፓን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ግንኙነቱን አጠናክሮ በመቀጠል የቶኩሹማ ዩኒቨርሲቲን የዳበረ የምርምር ልምዶችን መሰረት ያደረገ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡ ከጃፓኖች በርካታ ልምዶችን መቅስም እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ፕሮፌሰር አፈወርቅ ጠንካራ የስራ ባህላቸው ለኢትዮጵያውያን መልካም ተሞክሮ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ የቶኩሹማ ዩኒቨርሲቲ በአቅም ግንባታው ዘርፍ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰው ኃይል ስልጠና ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣ በቀጣይም አጫጭር ስልጠናዎችንና የ3ኛ ዲግሪ የትምህርት እድሎች እንዲመቻቹ የተጠናከሩ ስራዎች እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ ጃፓን ሀገር ከሚገኙ የሮተሪ ክለብና ከጃይካ ፕሮጀክት ጋር የተጠናከረ ግንኙነት እንዲመሰርት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጥረቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ እንደፕሮፌሰር አፈወርቅ ገለጻ 11 አባላት ያሉት የጃፓን የልኡካን ቡድን ወደ ጎንደር ከተማ ለመምጣት ያደረገው ጥረት ባይሳካም በአዲስ አበባ በነበረው ቆይታ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ግንኙነቱን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል፡፡ “የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ግንኙነቱን ዳግም አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የስምምነት ሰነዶችን በማዘጋጀት በቅርቡ እንፈራረማለን “ ብለዋል፡፡ “ጃፓን በህክምናው ዘርፍ የላቀ እውቀትና ቴክኖሎጂ ያላት አገር ናት” ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ ግንኙነቱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን አቅም ለማሳደግ አጋዝ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) በኢትዮጵያ በርካታ የልማትና የአቅም ግንባታ ድጋፎች ማበርከቱን የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዛዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ናቸው፡፡ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ታስቦ በጃፓኖች ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን “ሳኩራ” የተባለውን ብሔራዊ የዛፍ ዝርያ ከስድስት ዓመት በፊት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመታሰቢያነት መተከላቸውንና 25 ችግኞችን በልዩ ሁኔታ ለመንከባከብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።