በወረዳዉ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመረቁ

59
ሶዶ ነሐሴ 5 /2011 በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ ከ15 ሚሊዮን በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ። በሕዝብና በመንግሥት ተሳትፎ ተገንብተው ለአገልግሎት ከበቁት መካከል የወረዳው አስተዳደርና ለተለያዩ ተቋማት ለቢሮና ለማህበራዊ አገልግሎት መስጫነት የሚውሉ ህንጻዎችና የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ይገኙበታል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ፕሮጀክቶቹን ከመረቁ በኋላ እንደተናገሩት መንግሥት የሕዝብን የልማት ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በወረዳው ለምረቃ የበቁት ፕሮጀክቶች ሕዝብና መንግሥት ተጣምረው ሲንቀሳቀሱ ውጤታማ እንደሚሆኑ ማሳያ እንደሆኑ አመልክተው፣የልማት ሥራዎችን በተባበረ አቅም ተጠቅሞ ለመፈጸምና ተጠቃሚ ለመሆን ጥረቱ እንዲጠናከር አሳስበዋል። የዳሞት ወይዴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተመስገን ታደሰ በበኩላቸው ግንባታቸው የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች የወረዳው መሥሪያ ቤቶችን የቢሮ እጥረት ከማቃለል ባለፈ ምቹ የስራ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ አመልክተዋል፡፡ የተሳለጠ፤ፈጣን፤ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በአንድ ማዕከል ለማህበረሰቡ በማቅረብ የተጀመረውን የመልካም አስተዳደርና የፐብሊክ ሰርቪሱን ሪፎርም ለመተግበር እንደሚያስችሉም ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ጥራትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ የወረዳው አስተዳደርና ነዋሪዎች ያደረጉት ትብብር ለቀጣይ ሥራዎችም የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ተናግረዋል። በወረዳው የበዴሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ታደመ ተሰማ ሕዝቡ ፍላጎቱን የሚያዳምጡ አመራሮች በማግኘቱ ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ አጠናቅቆ ለአገልግሎት አብቅቷል ብለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም