በበጎ ፈቃደኞች በሚሰጥ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ተጨማሪ ክህሎት እያገኙ መሆኑን ተማሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፈቃደኞች በሚሰጥ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ተጨማሪ ክህሎት እያገኙ መሆኑን ተማሪዎች ተናገሩ
ነሐሴ 5/2011 በአዲስ አበባ በክረምት በጎ ፈቃደኞች እየተሰጠ ባለው የማጠናከሪያ ትምህርት ተጨማሪ የህይወት ክህሎት እያገኙ መሆኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
የከተማዋ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ በበኩሉ በበጎ ፈቃድ የትምህርት አገልግሎቱ ለ53 ሺህ ተማሪዎች እየተሰጠ መሆኑን ገልፅዋል፡፡
የ8 ተኛ ክፍል ተማሪ ሄርሜላ ስዩም እንዳለችው ክረምት ትምህርት ቤት በሚዘጋበት ግዜ መፅሃፍ የማንበብ ና እድሉን ስታገኝ ደግሞ የመማር ፍላጎት አለኝ ትላለች።
በዚህ ክረምትም ለቀጣይ አመት የሚያግዛትን ማጠናከሪያና በተጓዳኝ የስነጥበብ ትምህርት እየተከታተለች ሲሆን “ስለሃገሬ ባህልና ለራሴም፣ ለቤተሰቤም እንድጠቅም ምን ማድረግ እንዳለብኝ እውቀት አግኝቼበታለሁ” ብላለች፡፡
ተማሪ ቅዱስ ያሬድ በተያዘው አመት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና መውሰዱንና በክረምቱ በበጎ ፍቃደኞች የሚሰጠውን የቲያትር ትምህርት እየወሰደ መሆኑን ገልፆ፤ ስለባህል፣ ኢትዮጵያዊነት እና ጥሩ ስነ ምግባር መማሩን ተናግሯል፡፡
“ወደ ፊት ስለባህሌና ኢትዮጵያዊነት መግለፅ የምችለውን ነገር ተምሬያለሁ”የሚለው ተማሪ ቅዱስ አሁን ላይ በነፃ ያገኘው ትምህርት ወደ ፊት በጎፍቃድ ለመስጠት እንዳነሳሳው ይገልፃል፡፡
ለቀጣይ አመት የሚረዳትን ትምህርት እየተከታተለች መሆኑን የተናገረችው የ7ኛ ከፍል ተማሪ ገነት ኤፍሬም በበኩሏ፤ መምህራኖቿ ስለ ጥሩ ስነ-ምግባርና ትልቅ ቦታ ስለመድረስ እንደሚመክሩዋቸውና “በመማራችን ስነምግባራችን የተሻለ ሆኗል፤ በሰው ዘንድም ተወዳጅ እንሆናለን” ብላለች።
በዳግማዊ ሚኒሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤት የበጎ ፍቃድ አስተባባሪ ወጣት ነፃነት ተስፋዬ እንዳለው በክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ተማሪዎችም ሆኑ በጎ ፍቃደኛ አስተማሪዎች የህይወት ልምድ ያገኛሉ፡፡
በጎ ፍቃደኞቹ ለተማሪዎች ባላቸው ቅርበት ልምዳቸውን ያካፍላሉ ያለው ወጣቱ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ኢትዮጵያዊነትንና አብሮ መኖርን የተለማመዱ በመሆኑ ያላቸውን ልምድ ያካፍላሉ ብሏል።
ከቀለም ትምህርት ባሻገር ለታዳጊዎች የጤና ፣ የግእዝ እንዲሁም በሂሳብና ፊዚክስ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲያገኙ ና በሳምንት አንድ ቀን የወላጅ ተወካዮች ምክር እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ነው የተናገረው።
ተማሪዎች ክረምትን በትምህርት ማሳለፋቸው ከመጥፎ ድርጊት እንዲርቁ፣ አብሮነትን እንዲያዳብሩና በጋ ላይ የሚጠቀሙበት የአጠናን ዘዴና ከትምህርት እንዳይርቁ ያግዛቸዋልም ብሏል፡፡
በዚህ ክረምት የትምህርት ቤቶች እድሳት የተፈለገውን ያህል የተማሪ ቁጥር እንዳያስተምሩ እንዳደረጋቸው የተናገረው አስተባበሪው፤ እድሳታቸው በተጠናቀቀ ክፍሎች በመዘዋወር አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ብሩክ አበበ እንደተናገሩት በከተማዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የሰብአዊ አገልግሎት፣ደም ልገሳ፣ አካባቢ ፅዳት፣ ችግኝ ተከላ እና የትራፊክ ደህንነት አገልግሎት እየተሰጠ ነው ፡፡
በዚህ አገልግሎትም ከ5 -8ኛ ክፍል ያሉ 53 ሺህ 426 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየወሰዱ መሆኑን የገለፁት ሃላፊው ትምህርቱ በ2 ሺህ 423 በጎ ፍቃደኞች እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
“ታዳጊዎቹ የሚያስተምሯቸው በጎ ፍቃደኛ እንደሆኑ ስለሚያውቁ የእነሱን አርአያ በመከተል ታናናሾቻቸውን የማስተማር ፍላጎት ያድርባቸዋል”ያሉት ኃላፊው ፤ በጎ ፈቃደኝነት በተግባር አእምሮን የመገንባት ዝንባሌ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በክረምት የበጎፈቃድ ትምህርት ተማሪዎች በትያትርና ሙዚቃ የሃገር ፍቅርን፣ አብሮነትን እንደሚያንፀባርቁና በአንፃሩም ስለሌብነት፣ ሐሰት ና ክፋት የሚያወግዙ እንደሆነም ነው የተናገሩት።፡፡
ወደ ፊት ከአካዳሚ ትምህርቶች ባለፈ የስነምግባር ትምህርትን ለመስጠት በእቅድ ተይዞ እንደሚሰራ ያሉት አቶ ብሩክ ሁሉም ማህበረሰብ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡