የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ150 ሚሊየን ብር ወጪ የእሽግ ዉሃ ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ150 ሚሊየን ብር ወጪ የእሽግ ዉሃ ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው
ደብረ ብርሃን ነሐሴ 5/ 2011 የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በ150 ሚሊየን ብር ወጪ የእሽግ ዉሃ ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው። ለፋብሪካው ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት ወቅት እንደተናገሩት ፋብሪካው የሚከናወነው የኮሚቴውን ገቢ ለማሳደግ ነው ። በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ጨኪ ቀበሌ በአምስት ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባው ፋብሪካ ”የኦሊምፒክ ውሃ” የሚል ስያሜ ያለው የታሸገ ውሃ ለገበያ ያቀርባል። በግንባታው ወቅትም ሆነ ምርት ሲጀምር የአካባቢውን አርሶ አደሮች እንደሚያሳትፍ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል። የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኢንጂነር ራውደስ ጳውሎስ በበኩላቸው ፋብሪካው በቀን 72 ሺህ ሊትር ውሃ እንደሚያመርት ተናግረዋል። በዚሀም ከ100 እስከ 200 ለሚደርሱ ሰዎች ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። የአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደር በዙ ብሩ በበኩላቸው በአካባቢው የግል ባለሀብቶች በእሽግ ውሃ ምርት በስፋት እየገቡ ቢሆንም፤ ኮሚቴው የሚያቋቁመው ፋብሪካ የስፖርት ማህበረሰብ ሀብት በመሆኑ እንደ ራሳችን ሃብት እንከባከበዋለን ብለዋል። በደብረ ብርሃን ከተማ የኮሚቴውን 44ኛ መደበኛ ጉባዔ ያካሄዱት ተሳታፊዎች ፋብሪካው በሚያርፍበት ሥፍራ ችግኞች ተክለዋል።