በካዎ ኮይሻ ወረዳ መኖሪያ ቤት ተደርምሶ የአባወራው ህይወት አለፈ

138
ሶዶ ነሐሴ 5/2011 በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ በደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት በተፈጠረ የመኖሪያ ቤት የመደርመስ አደጋ የአባወራው ህይወት ማለፉንና በልጃቸው ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ። አደጋው የደረሰው ትናንት እኩለ ቀን አካባቢ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲጥል የቆየው ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት የአንድ ቤተሰብ  መኖሪያ ቤት በመደርመሱ ነው፡፡ በወረዳው ኦፋ ሂራ የገጠር ቀበሌ እኩለ ቀን አካባቢ አደጋው ድንገት በመድረሱ በመኖሪያ ቤታቸው ከልጃቸውጋር የነበሩ አባወራ ህይወት ሊያልፍ ችሏል። በአከባቢው ማህበረሰብ ጥረት ሊድን የቻለው 14 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጃቸው ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶበት በወረዳው ላሾ ጤና  ጣቢያ የህምና እርዳታ እየተደረገለት መሆኑን የካዎ ኮይሻ ወረዳ ወንጀል መርማሪ ሻምበል ምትኩ ዘውዴ ለኢዜአ ገልጸዋል። ሟች በአከባቢዉ ሞዴል አርሶ አደር እንደነበሩ አመልክተው ለአከባቢዉ አርሶ አደሮች የሚያቀርቡት ምርጥ ዘር፤ የተከማቸ እህልና ሌሎች ንብረቶች ጨምሮ ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን አስረድተዋል፡፡ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስራት ሴታ በበኩላቸው “ጉዳቱ የደረሰበትን ቤተሰብ በዘላቂነት ለማቋቋም አስተዳደሩ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል “ብለዋል፡፡ አካባቢው ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚከሰቱበት በመሆኑ ለምን ጥንቃቄ አልተወሰደም ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የነበረው ስጋት ተከትሎ ከ25 በላይ አርሶ አደሮችን ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር መግባባት ላይ በመድረስ እየተሰራ ባለበት በድንገት የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁንም እነዚህ አርሶ አደሮች ከአካባቢው ወጥተው ወደ ተሻለ ቦታ በመስፈር የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ የሚደረቸው መሆኑን ገልጸው ከስጋት ነጻ ሆነው በዘላቂነት የሚኖሩበት አካባቢ የማዛወር ስራ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም