ቀጥታ፡

የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጀመረ

ነሀሴ 5/2011 ኅብረተሰቡ ኦቲዝም ላይ ያለውን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ በየሁለት ወሩ የሚካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተጀመረ። የጤና ሚኒስቴር ከኒያ ፋውንዴሽን ጆይ የኦቲዝም ማዕከል ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀው ብሄራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ትናንት ተካሂዷል። በመድረኩ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆችና ወላጆቻቸው፣ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። ኦቲዝም ከነርቭና አንጎል አሰራር ሂደት ጋር ግንኙነት ያለው የእድገት እክል ሲሆን ኦቲዝም ያለበት ሰው አንጎል አሰራር ከህመሙ ነጻ ከሆነ የኅብረተሰብ ክፍል የተለየ ያደርገዋል። የሚኒስቴሩ የህክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ልዩ አማካሪ አቶ ኢሳይያስ መለሰ እንዳሉት በአገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ለሁሉም ኀብረተሰብ ተደራሽ  የማድረግ  ስራ እየተሰራ ነው። ይህም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ከሌላው ኀብረተሰብ ጋር ያለአድልዎ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው። በኦቲዝም ላይ በሚፈለገው ልክ  'አልተሰራም' ያሉት አቶ ኢሳይያስ ሚኒስቴሩ ከ2010 ጀምሮ እየተገበረ ባለው የአምስት ዓመት እቅድ ልዩ ፍላጎት ያላቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል። ባለፉት ሶስት ወራት  የሆስፒታሎች አወቃቀር ልዩ ፍላጎት ያላቸውን የኀብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ እንዲያደርግ ሆኖ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሚኒስቴሩ በኒያ ፋውንዴሽን ለሚገነባው የኦቲዝም ልህቀት ማዕከል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የኀብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ለማሳደግ የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በየሁለት ወሩ ይካሄዳል ብለዋል። የኒያ ፋውንዴሽን መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ጆይ የኦቲዝም ማዕከል ላለፉት 18 ዓመታት የኀብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና ኦቲዝም ላለባቸው ልጆች ትምህርትና ስልጠና በመስጠት መቆየቱን አስታውቀዋል። ማዕከሉ ከአሁን በኋላ በየሁለት ወሩ አገር አቀፍ የጋራ መድረክ በቋሚነት እንደሚያካሂድና ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ፣ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች፣ ወላጆችና ባለሙያዎች መሳተፍ እንደሚችሉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦቲዝም ሶሳይቲ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ወላጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች የሚያነሱበት እንደሚሆንም ተናግረዋል። ማዕከሉ 80 ልጆችን በማሰልጠን ላይ ሲሆን በቀጣይ ሊገነባ የታሰበው የልህቀት ማዕከል አቅሙን ወደ 400 ልጆች እንደሚያሳድገው አብራርተዋል። 'የአንድ ቀን ገቢ ለኒያ' በሚል በሁሉም ባንኮች በተከፈቱ የአካውንት ቁጥሮች ሁሉም ሰው ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ የተሳተፉ ወላጆችና ቤተሰቦችም መድረኩ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና ተሞክሮ ለመለዋወጥ እንደሚረዳቸው ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም