ሕዝበ ሙስሊሙ በአረፋ በዓል ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቹን እንዲያስባቸው ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝበ ሙስሊሙ በአረፋ በዓል ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቹን እንዲያስባቸው ተጠየቀ
አዲስ አበባ ኢዜአ ነሃሴ 4/ 2011 ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ አረፋን በዓል ሲያከብር በወቅታዊ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቹን በማሰብ እንዲሆን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አሳሰበ። ጉባዔው መላውን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 440ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል አደረሳችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል። መልካም ምኞቱን ባስተላለፈበት መግለጫም ሙስሊሙ ህብረተሰብ በዓሉን ማክበር ያለበት በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብና ያለውን በማካፈል እንዲሆን አስገንዝቧል። በተለይም በወቅታዊ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ እንዲሆን ነው ያሳሰበው። በዓሉ ህዝበ ሙስሊሙ አንድነቱንና ወንድማማችነቱን በማጠናከርና ተፈጥሮ የነበረውን መከፋፈል በመፍታት ሁሉን ያካተተ ጠንካራ መጅሊስ እንዲኖር የሚያስችል ስራ በተጀመረበት ወቅት መከበሩ ከቀደሙት ዓመታት የተለየ እንደሚያደርገው ገልጿል። ይህም በመጅሊሱ ታሪክ የነበሩ ክፍተቶችን በመፍታት ለህዝበ ሙስሊሙ ሁለንተናዊ አገልግሎት የሚሰጥ ኢስላማዊ ተቋም እንዲፈጠር የሚያስችል መሆኑን እንደሚገነዘብ ጉባዔው አስታውቋል። ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር በመተባበር የሠላምና የመከባበር እሴት ግንባታን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም የጉባኤው መግለጫ ያትታል። የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል አላህ የነብዩ ኢብራሂምን ፍቅርና እምነት ለመፈተን ልጃቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዘበት፤ እርሳቸውም ለፈጣሪ የነበራቸው እምነትና ፍቅር ፍፁም ነበርና የሚወዱት ልጃቸውን እስማኤልን ወደ መሰዊያው ያቀረቡበት ነው። ነገር ግን ታዛዥነታቸውን የተረዳው ፈጣሪ በምትኩ ሙክት በግ አዘጋጅቶላቸው በጉን በማረድ ለፈጣሪ መስዋዕት አቀረቡ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ዕለቱ የዕርድ ወይም የኡዱህያ ቀን ተብሎ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።