ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርታዊ ውድድር ትግራይ በ16 የስፖርት ዓይነቶች ይሳተፋል

መቐለ (ኢዜአ) ነሃሴ 04 ቀን 2011 በአገር አቀፍ ደረጃ በአርባ ምንጭ ከተማ በሚካሄደው የታዳጊ ወጣቶች ስፖርታዊ ውድድር የትግራይ ክልል በ16 የስፖርት ዓይነቶች እንደሚወዳደር የክልሉ ስፖርትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ገለፀ። በቢሮው የህዝባዊ መሰረት ስፖርት እድገት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ካህሱ ዜናዊ ትናንት ለኢዜአ እንደገለጹት በአገር አቀፍ ደረጃ በአርባ ምንጭ ከተማ ከነሀሴ 11 እስከ ነሃሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም የብቃት ምዘና ስፖርታዊ ውድድር ይካሄዳል፡፡ በዚሁ ውድድር የትግራይ ክልል በሁለቱም ፆታዎች ለመሳተፍ ዝግጅቱን አጠናቅቋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተዘጋጁት 17 ዓይነት የስፖርት ውድድሮች መካከል የትግራይ ክልል በ16ቱ የውድድር አይነቶች ይሳተፋል ። ክልሉ ከሚሳተፍባቸው የስፖርት ዓይነቶች መካከል የእግርና መረብ ኳስ ፣ አትሌቲክስ ፣ ብስክሌትና ቴኳንዶ ይገኙበታል፡፡ ክልሉን ወክለው በውድድሩ የሚሳተፉ 534 ታዳጊ ወጣቶች በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ወደ ቦታው አንደሚጓዙም ዳይሬክተርዋ ተናግረዋል ። ከተወዳዳሪ ታዳጊ ወጣቶች መካከል ከሰሃርቲ ሳምረ ወረዳ የመጣች ወጣት ሳምራዊት መብራህቱ በሰጠችው አስተያየት በውድድሩ ክልልዋን ለማስጠራት በቂ ዝግጅት አድርጋለች ። ታዳጊ ወጣት ታምሩ አለም በበኩሉ የሚሳተፍበት የእግር ኳስ ውድድር ብቃቱን ለማሳየትና በክለብ ለመታቀፍ መልካም አጋጣሚ ይፈጥርልኛል የሚል ተስፋ እንዳሳደረበት ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም