የሂጂራ ኢድል አድሃ በዓል የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የሂጂራ ኢድል አድሃ በዓል የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ይከበራል

ባህር ዳር (ኢዜአ) ነሀሴ 3 ቀን 2011- ህዝበ ሙስሊሙ የሂጂራ ኢድል አድሃ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ፣ የታመሙና የታሰሩትን በመጠየቅ ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አሳሰበ። ምክር ቤቱ ከነገ በስቲያ የሚከበረውን 1ሺህ 440ኛውን የሂጂራ ኢድል አድሃ በዓልን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሀመድ በሰጡት መግለጫ በዓሉ የሚከበረው በሶላት ስግደትና ዕምነቱ በሚፈቅደው መሰረት የእርድ ስርዓት በመከወን ነው። ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትንና የተራቡ ወገኖች በመርዳት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል። ከሚፈፀመው እርድም ሁለት ሦስተኛው ለተቸገሩ ወገኖች፣ ለጎረቤትና ለቤተዘመድ፣ ቀሪው ደግሞ ለቤተሰብ እንዲሆን ዕምነቱ በሚያዝዘው መሰረት እንዲከናወነም አስገንዝበዋል። "በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ አላስፈላጊ ግጭቶች ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መደገፍና ወደቀደመ ቄያቸው ተመልሰው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ሙስሊሙ ህብተሰብ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል። ሰላም ከሌለ ወጥቶ መመለስ፣ ማምለክ፣ ሰርቶ መበልፀግና ልጅ ወልዶ ማሳደግ እንደማይችል ህዝበ ሙስሊሙ ተረድቶ ለሰላሙ ዘብ መቆምና ሰላሙን ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል። ይህም ኢትዮጵያዊያን በዓለም አደባባይ የሚታወቁበትና ለዘመናት የዘለቀውን የአብሮነትና የመተሳሰብ እሴት ይበልጥ በማገጎልበት ጭምር መሆን እንዳለበት ነው ሼህ ሰይድ መሀመድ ያሳሰቡት። "ለሀገሪቱ ህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ዱአ በማድረግም በዓሉን ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና ከሌሎች የዕምነቱ ተከታይ ወገኖቻችን ጋር በጋራ አብረን ልናሳልፍ ይገባል" ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የታመሙና በህግ ጥላ ስር የዋሉ ወገኖችን በመጠየው በዓሉን ማክበት እንደሚገባ ገልጸው በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማክበርም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። የዕምነቱ ተከታዮችም በዓሉ በጋራ በሚከበርበት ዕለት ወደሶላት ቦታ ሲመጡ ስለትና ተቀጣጣይ ነገር ይዘው ከመምጣት እንዲቆጠቡ ሼህ ሰይድ መሀመድ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። በዓሉ ከነገ በስቲያ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ጥዋቱ 2 ሰዓት ድረስ እንደሚከበርም ታውቋል። ምክር ቤቱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር በዕለቱ የዕምነቱን ተከታዮች ወደሶላት ቦታው የሚያጓጉዙ 12 የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እንዲዘጋጁ ማድረጉም ታውቋል።