የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሐምሌ ወር 51 ሺህ ቶን በላይ ምርት በ2 ነጥብ 92 ቢሊዮን ብር አገበያየ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሐምሌ ወር በነበሩት 23 የግብይት ቀናት 51 ሺህ ቶን በላይ ምርት በ2 ነጥብ 92 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ገለጸ። ምርት ገበያው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ 32 ሺህ 291 ቶን ቡና፣ 11 ሺህ 273 ቶን አኩሪ አተር፣ 5 ሺህ 817 ቶን ሰሊጥ፣ 1 ሺህ 765 ቶን ነጭ ቦሎቄና 28 ቶን አረንጓዴ ማሾ በሐምሌ ወር አገበያይቷል። በዚህም በጠቅላላው 51 ሺህ 174 ቶን ምርት በ2 ነጥብ 92 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡ በተጠቀሰው ወር ቡና 63 እና 81 በመቶ በግብይት መጠንና ዋጋ ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡ በተመሳሳይም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና በግብይት መጠንና ዋጋ 67 በመቶ በመያዝ ድርሻ ሲኖረው ካለፈው ወር ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 23 እና 30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በወሩ 20 ሺህ 326 ቶን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ያልታጠበ ቡና በ1 ነጥብ 52 ቢሊየን ብር ሲገበያይ ከዚህ ውስጥ በግብይት መጠን የኢሉአባቦራ ቡና 22 በመቶ፣ የጊምቢ 19 በመቶ፣ የቄሌም ወለጋ 13 በመቶ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ምርት ገበያው ገልጿል። እንዲሁም 1 ሺህ 311 ቶን ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የታጠበ ቡና በ92 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን የሲዳማ ቡና የግብይቱን 50 በመቶ ይዟል፡፡ የይርጋጨፌና የሊሙ ቡና 23 እና 13 በመቶ ድርሻ በመያዝ ይከተላሉ፡፡ የታጠበ 3 ሺህ 676 ቶን ልዩ ቡና በ297 ነጥብ 83 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ 1 ሺህ 056 ቶን ያልታጠበ ልዩ ቡና 113 ነጥብ 98 ሚሊዮን ብር ግብይቱ ተከናውኗል፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ 5 ሺህ 923 ቶን ቡና በ 364 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ የቡና ግብይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 66 እና 73 በመቶ በመጠንና በዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ አማካይ የቡና የግብይት ዋጋ በሰባት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁሟል። በሐምሌ ወር ግብይት 11 ሺህ 273 ቶን አኩሪ አተር በ170 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የጎጃም አኩሪ አተር 49 እና 48 በመቶ በዋጋና በመጠን የግብይቱን ድርሻ መያዙን የምርት ገበያው ገልጿል። እንዲሁም 5 ሺህ 817 ቶን ሰሊጥ በ320 ነጥብ 17 ሚሊዮን ብር ሲገበያይ፣ ነጭየሑመራ/ጎንደር ሰሊጥ 72 እና 73 በመቶ በመጠንና በዋጋ በመያዝ ተገበያይቷል፡፡ የሰሊጥ ግብይት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በዋጋ 69 በመቶ ጭማሪ ሲያሳይ በመጠን 57 በመቶ ጨምሯል፡፡ አማካይ የሰሊጥ የግብይት ዋጋም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ8 ነጥብ 85 ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ 1 ሺህ 765 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ35 ነጥብ 45 ሚሊዮን ብር ሲሸጥ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር መጠኑ የ2 ነጥብ 14 ጭማሪ አሳይቷል። ነገር ግን በዋጋ በ0 ነጥብ 27 በመቶ ቅናሽ እንዳሳየ ተገልጿል። በሐምሌ ወር 28 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ791 ሺህ ብር መገበያየቱን የምርት ገበያው ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ለኢዜአ የላከው መግለጫ ያሳያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም