''በአሁን ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በሰላም የመኖር ነው''- ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ - ኢዜአ አማርኛ
''በአሁን ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በሰላም የመኖር ነው''- ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ
ኢዜአ ነሀሴ 3/2011 ''በአሁን ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ በሰላም የመኖር ነው'' ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ተናገሩ። ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ይህን ያሉት ዛሬ የሰላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን አስመልክቶ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የ7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ተሳትፈዋል። ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው በዘርና በጎሳ ተከፋፍሎ ወደ ግጭት የመግባት አባዜ ከየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ ጋር አይስማማም። ከውጭ አገር ጦር መሳሪያ አስገብቶ በወገን ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ማፈናቀልና መግደል 97 በመቶ ያህል የሃይማኖት ተከታዮች አላት በምትባል አገር የማይጠበቅ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑንም አመልክተዋል። የሃይማኖት አባቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በእኩይ ተግባር ከመሰማራት ተቆጥበው ለተከታዮቻቸው ዓረዓያ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። ''በአሁን ጊዜ የኢትዮያውያን ጥያቄ በሰላም የመኖር ነው'' ያሉት ካርዲናሉ በአገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች ሰላምን ለማስፈን በተለይ የሃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። የ7ኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን ፕሬዚዳንት ፓስተር ተመስገን ቡልቲ በበኩላቸው ''በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሃይማኖት ተቋማት እገዛ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል'' ብለዋል። የሰላም ጉዳይ ለሌላ ሰው ተብሎ የሚተው ባለመሆኑ በተለይ የሃይማኖት አባቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ቀን ከሌሊት ተግተው መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን (ቀሲስ) ታጋይ ታደለ የሃይማኖት ተቋማት በመልካም ስነ-ምግባርና በመልካም አስተዳደር ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ አንስተዋል። በአሁን ጊዜ በአገሪቷ እየታዩ ያሉ ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ያነሱት ጠቅላይ ጸሃፊው፤ የመልካም አስተዳደር እጦት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች እንዲፈጠሩ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የመልካም አስተዳደ መርህዎችን ከሃይማኖት እሴቶች ጋር በማስተሳሰር ማስተማር እንደሚገባ በውይይቱ ተገልጿል።