ቀጥታ፡

ኢትዮ-ህንድ ቢዝነስ ፎረም በመጪው ሰኞ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ኢዜአ ነሀሴ 3/2011 የኢትዮ-ህንድ ቢዝነስ ፎረም ከሁለት ቀናት በኋላ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ፎረሙ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን 30 የኢትዮጵያ እና 10 የህንድ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው እንደገለጹት፤ በፎረሙ የሚሳተፉ ኩባንያዎች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በምግብና ወተት ማቀነባበርና በኢንፎርሜሽን ዙሪያ የተሰማሩ ናቸው። ከኩባንያዎቹ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የውሃና መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተወካዮች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። ይህም ፎረም በአገሪቱ ያለውን ምቹ ሁኔታ በማስተዋወቅ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማሳደግን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል። ላለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያና የህንድ የንግድ ግንኙነት በአማካይ 20 በመቶ የደረሰ ሲሆን ፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 የሁለቱ አገራት የንግድ ፍሰት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ያሉ ከ500 በላይ የህንድ ኩባንያዎች በ10 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለ50 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል። በተጨማሪም ሁለቱ አገራት ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ በአየር መንገድ አገልግሎት፣ በኢኮኖሚና ሳይንስ ዘርፍ፣ በባህልና በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና በግብርና ምርምር በትብብር ለመስራት የጋራ ስምምነት አላቸው። በሌላ ዜና የኢትዮጵያና ኬንያ ተጎራባች ማህበረሰቦች የባህል ቱሪዝም ፌስቲቫል በኬንያ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። ፌስቲቫሉ ከነሐሴ 8 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የሁለቱ አገሮች ባህሎችና እሴቶች ይቀርባሉ ተብሏል። ፌስቲቫሉ በጋራ ድንበር አካባቢ የሚደረጉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ ስራዎች ለሰላምና ለአብሮነት መጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለውም ታምኖበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም