ኢትዮጵያና ጃፓን የ82 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ጃፓን የ82 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ
ኢዜአ ነሀሴ 3/2011 ኢትዮጵያና ጃፓን ለህክምና መሳሪያዎች ግዥና ለጃፓን መንግስት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት መርሃ ግብር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ82 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ተፈራረሙ። ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አድማሱ ነበበና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ዳሱኪ ማታሱናጋ ናቸው። አቶ አድማሱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የፕሮጀክቱ ዓላማ መንግስት የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል እያደረገ የሚገኘውን ያላሰለሰ ጥረት መደገፍ ነው። ፕሮጀክቱ በዩኒቨርስቲዎችና የህክምና ስልጠና በሚሰጡ ሆስፒታሎች ለህክምና አገልግሎትና ለማስተማሪያ የሚሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን የማሰራጨት ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል። እንደ ሚንስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ አገሪቷ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው የልማት ስራዎች ጋር የተጣጣመ ነው ። የጃፓንና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትብብር ለበርካታ አመታት የዘለቀ መሆኑን የገለጹት አቶ አድማሱ፤ በጃፓን በኩል የሚደረገው የልማት ድጋፍም እየተስፋፋ መምጣቱንም አንስተዋል። ጃፓን የኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ ስራዎችን በመደገፍ ከአገሪቷ ዋና ዋና የልማት አጋሮች መካከል አንዷ መሆኗንም አክለዋል። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባደር ዳሱኪ በበኩላቸው ጃፓን ለኢትዮጵያ ከምታደርገው ድጋፍ ለጤናው ዘርፍ ቅድሚያ መስጠቷንና ይህም ድጋፍ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ በጤና፣ በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ፣ መሰረተ ልማት፣ ትምህርትና ሌሎች ዘርፎች ላይ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጃፓን የሚያደርጉት ጉብኝት የአገራቷን ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከሩ ረገድ የሚኖረውን ሚናንም ጠቁመዋል። የጤና ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ሳህራላ አብዱላሂ በበኩላቸው ግዥ ከሚከናወንባቸው የህክምና መሳሪያዎች መካከል እንደ ማይኮሮስኮፕ፣ ማሞግራፊ፣ ኢንዶስኮፒና ሌሎች እጥረት ያለባቸው መሳሪያዎች ይገኙበታል ብለዋል። ይህም የአገሪቷን የህክምና አገልግሎት የሚያሻሽልና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያጎለብት ነው ብለዋል።