ኮይካ በአማራ ክልል ስድስት ቀበሌዎች ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
ኮይካ በአማራ ክልል ስድስት ቀበሌዎች ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ስምምነት ተፈራረመ
ባህር ዳር 6/2010 የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ በአማራ ክልል ስድስት ቀበሌዎች ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር ተፈራረመ፡፡ በስምምነቱ መሠረት ኮይካ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በክልሉ ስድስት ቀበሌዎች በ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ያከናውናል፡፡ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የኮይካ ዳይሬክተር ያንግ አህ ዶህ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አይተነው እንዳሻው ፈርመዋል፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በስምምነቱ ወቅት እንደገለፁት ከተለያዩ ሀገራት የተሻሻሉ የአሰራር ልምዶችን በመቀመር የክልሉ አርሶ አደሮች ኑሮ ለማሻሻል እየተሰራ ነው። ከኮይካ ጋር የተደረገው ስምምነትም በአጭር ጊዜ ውጤት እንዲያመጣና ወደ ሌሎች ቀበሌዎች ልምዱ እንዲስፋፋ ለማድረግ የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል። የኮሪያ ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ /ኮይካ/ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ኘሮጀክት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ምትርሃና አባወረቃ ቀበሌዎች፣ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ወንጪት ቀበሌ፣ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ ሰገኒ ቀበሌና በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ ወረዳ ጨፋነን ቀበሌዎች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ቀበሌዎቹ የህብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤና ስነ-ምድራዊ አቀማመጥ መሰረት በማድረግ የተመረጡ ናቸው ተብሏል። በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ሁን ሚን ሊም በበኩላቸው ኮይካ ለማደግ ያላሳለሰ ጥረት የሚያደርጉ ሀገራትን ለመርዳት የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ”ኢትዮጵያ ለማደግ እየሰራችና በማደግ ላይ ያለች ሀገር በመሆኗ በሚያስፈልጓት ሁሉ ለመደገፍ ድርጅቱ ይሰራል” ብለዋል። የኮሪያና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከልማት ባለፈ የደም ዋጋ የተከፈለበት ግንኙነት ያላቸው መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ አገሪቱ መካከለኛ ገቢ ካለቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ያላሳለሰ ጥረት ኮሪያ ልምዷን ለማካፈልና ድጋፍ ለማድረግ ጠንክራ እንደምትሰራ ገልፀዋል፡፡ በእለቱ የተደረገው ስምምነትም ኮሪያ ከምንም ተነስታ ዛሬ ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ የረዳትን የገጠር ቀበሌ ልማት ስትራቴጂ ለማጋራት ስለሆነ ውጤቱም በአጭር ጊዜ የሚታይ ይሆናል ነው ያሉት። ስምምነቱ በአጭር ጊዜ በተመረጡ ቀበሌዎች ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ኮይካ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የኮይካ ዳይሬክተር ያንግ አህ ዶህ ናቸው። የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አይተነው እንዳሻው እንደገለጹት ስምምነቱ የገጠር ልማት ስትራቴጅ ዲዛይን ማድረግ ላይና የአመራርና የፈጻሚ አካላትን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት ያለመ ነው። ኮሪያዊያን እንዴት እንዳደጉ ልምድና ተሞክሯቸውን በተግባር ከማሳየት በተጨማሪ ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልገውን ወጭም ሙሉ በሙሉ ለመቻል መስማማታቸውን ገልፀዋል። ስምምነቱ ለአምስት ተከታታይ አመታት የሚቆይ ሲሆን ከዛ በኋላ መንግስት ተቀብሎ የሚያስቀጥለው ይሆናል ነው ያሉት። በስምምነቱ መሰረትም የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ሽግግር የሚያረጋግጡ አቅም ግንባታ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመንገድ ግንባታና ሌሎች የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተግበራት ይከናወናሉ ብለዋል። በስምምነቱ ላይ የክልሉን ርዕስ መስተዳደር ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ የስራ ኃላፊዎችና የኮይካ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።