የሰቆጣ ቃልኪዳንን በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የሰቆጣ ቃልኪዳንን በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ኢዜአ ነሀሴ 3 /2011 የሰቆጣ ቃልኪዳንን በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ። የሰቆጣ ቃል ኪዳን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ህጻናትን ከመቀንጨር ለመከላከል በሐምሌ ወር 2007 ዓ.ም ይፋ የተደረገ ቃልኪዳን ነው። የቃል ኪዳኑን የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ አስመልክቶ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ሁለተኛ ፎረም ትናንት ማምሻውን ተካሄዷል። ፎረሙ መንግስትና ባለድርሻ አካላት በሰቆጣ ቃል ኪዳን ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳድጉ ያለመ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በፎረሙ ላይ የ2012 ዓ.ም የሰቆጣ ቃል ኪዳን የሶስተኛ ዓመት ዕቅድን ይፋ አድርገዋል። ቃልኪዳኑ ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ መቀንጨር በስፋት በሚታይባቸው የአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በሰቆጣና በተከዜ ተፋሰስ በሙከራ ምዕራፍ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ 32 ወረዳዎች እየተተገበረ ይገኛል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰቆጣ ቃል ኪዳን በሙከራ ምዕራፍ ተግባር መቀንጨርን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። ቢሆንም ቃልኪዳኑ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች እምብዛም የተባለውን ያህል ስራ ማከናወን አለመቻሉን ተናግረዋል። በትግበራው ስራ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የቅንጅት አሰራር ክፍተት ያለበትና ስራዎች በተበታታነ መልኩ ሲሰሩ መቆየታቸው የሚጠበቀውን ያህል ላለመሰራቱ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል። ቃልኪዳኑ ይፋ ሲደረግ የነበረው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት አሁን ተቀዛቅዞ መታየቱና የስራው ባለቤትነት ስሜቱም ክፍተት የታየበት እንደሆነ ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት። የሀብት ማሳባሰበሳብ ስራው በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑና ለተለያዩ ስራዎች የሚያስፈልገው በጀት በበቂ ደረጃ አለመገኘቱንም አመልክተዋል። የከፋ ድህነት መገለጫ የሆነውን መቀንጨር መከላከል ዋንኛ አገራዊ ስራ ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። የመቀንጨር ችግርን ከመፍታት ያለፈ ስኬትና ውጤት እንደሌለ የገለጹት አቶ ደመቀ መቀንጨርን ለማስወገድ ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የሰቆጣ ቃልኪዳን ውጤታማ እንዲሆን በተጠናከረና መሬት በነካ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። "መቀንጨርን ማስወገድ ዜግነትን መታደግ ነው፤ መቀንጨርን ማስወገድ ለዘላቂ ልማት መሰረት መጣል ነው" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለጋነት ዕድሜ በህጻናት ላይ ጉዳት የሚያደርሰው መቀንጨርን ለመከላከል ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። ተስፋ የሰነቀና በአገሩ የሚኮራ ዜጋ ለማፍራት መቀንጨርን መከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለውና እንደ ቁልፍ የልማት አጀንዳ ሊታይ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። የሰቆጣ ቃልኪዳን ከሙከራ ምዕራፍ ወደ ተሟላ የትግበራ ምዕራፍ ለማሸጋገር የወረዳዎችን አቅም ማጎልበት፣ የሚመደበውን በጀት በአግባቡ መጠቀምና የግልጽነት አሰራር ማስፈን፣ የስራ ድርሻ ክፍፍልን በግልጽ ማስቀመጥ፣ የተቀናጀ የዕቅድ አወጣጥና የትግበራ ባለቤትነትን በአግባቡ መለየትና ማህበረሰባዊ ንቅናቄን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል። ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም የሰቆጣ ቃልኪዳንን አስመልክቶ በተካሄደው የመጀመሪያው ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፎረም ላይ የተሰጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም እና የሰቆጣ ቃልኪዳን የ2012 ዓ.ም የሶስተኛ ዓመት እቅድ ላይ ገለጻ ተደርጓል። ገለጻውን ያቀረቡት የፌዴራል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ የበጀት እጥረትና ከፌዴራል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ባለቤት ሆነው በቅንጅት አለመስራታቸው የሰቆጣ ቃልኪዳንን አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዳደረገው ጠቅሰዋል። ያሉትን ችግሮች ለመፍታት በጥር 2011 ዓ.ም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ፎረም በማዘጋጀት አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት ቃልኪዳኑን በፍጥነት መተግበር እንደሚያስፈልግ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የመንግስት አመራሮች ቃልኪዳኑ በሚተገበርባቸው ወረዳዎች በማምራት እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች በመመልከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያያታቸውን አመልክተዋል። በወረዳዎቹ ያሉትን ችግሮች በመለየት ቅድሚያ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮች መለየታቸውንም ጠቅሰዋል። የውሃ እና የምግብ አቅርቦት፣ የመንገድ ተደራሽነትና የዳስ ትምህርት ቤቶችን ወደ ቋሚ ትምህርት ቤቶች መቀየር ላይ ችግሮች በዋነኛነት የተለዩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ከወረዳዎች የተደረገው ውይይት ከዚህ በፊት ከዘርፍ መስሪያ ቤቶች ፍላጎት በመነሳት ቃልኪዳኑን ለመተግበር ሲከናወን የነበረውን አሰራር ያስቀረ ነው ብለዋል። የቃልኪዳኑ የ2012 ዓ.ም ትግበራ የተለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ በጀት መመደቡንና በአማራ ክልል 27 በትግራይ ክልል 13 ወረዳዎች የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። የፌዴራል መንግስት ለ2012 ዓ.ም የስራ ማስኬጃ 477 ሚሊዮን ብር መመደቡንና በአጠቃላይ ለ2012 ዓ.ም ስራዎች 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የተቀረው በጀት ቃልኪዳኑን ተግባራዊ የሚያደርጉት 10 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከአጋር ድርጅቶች እንደሚሰበሰብም አመልክተዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም ለስራ ማስኬጃ የሚያደርገውን ድጋፍ ይፋ እንደሚያደርግም ጠቅሰዋል። የሰቆጣ ቃልኪዳን የሙከራ ምዕራፍ ትግበራ እስከ 2013 ዓ.ም እንደሚቆይና ከ2013 እስከ ከ2017 ዓ.ም ቃልኪዳኑን የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ 38 በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በታች ህጻናት የመቀንጨር ችግር እንዳለባቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።