ቀጥታ፡

የአረፋ በዓል ሲከበር አቅመ ደካሞችን በማሰብና በመደገፍ ሊሆን ይገባል - ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር

አዲስ አበባ ኢዜአ  ነሀሴ 3 /2011 የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል እምነቱ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካሞችን በማሰብና ያለው ለሌለው በማካፈል እንዲያከበር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢድሪስ አሳሰቡ። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ዑመር ኢድሪስ 1 ሺህ 440ኛውን የአረፋ በዓል አስመልክተው ለሕዝበ ሙስሊሙ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢድ አል አድሃ አረፋ አላህ የነብዩ ኢብራሂምን ፍቅርና እምነት ለመፈተን ልጃቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዘበትን ዕለት ለማሰብ የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ነው። ነብዩ ኢብራሂም ለፈጣሪ የነበራቸው እምነትና ፍቅር ፍፁም ነበርና የሚወዱት ልጃቸውን እስማኤልን ይዘው ወደ መሰዊያው አቀኑ፤ ታዛዥነታቸውን የተረዳው ፈጣሪም በምትኩ ሙክት በግ አዘጋጀላቸው። እርሳቸውም በጉን በማረድ ለፈጣሪ መስዋዕት አቀረቡ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ዕለቱ የዕርድ ወይም የኡዱህያ ቀን ተብሎ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል። ይህን ታሪክ ለመዘከር በዓሉ "የመስዋዕትነት በዓል" ተብሎ እንደሚጠራ የእምነቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ፤ የእምነቱ ተከታዮችም የነብዩ መሃመድን ፈለግ ተከትለው በዕለቱ እርድ ይፈጽማሉ። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር ኢድሪስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ በዓሉን የተቸገሩትን በማሰብና በማካፈል በፍቅር ማሳለፍ ይገባል ብለዋል። ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብርም እምነቱ በሚያዘው መሰረት አቅመ ደካሞችን በማሰብ፣ ያለውን በማካፈልና በማስደሰት መሆን እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ አንድነትና ሠላምን ማስጠበቅ መሆኑን የጠቀሱት ሃጅ ኡመር እድሪስ "በሀገርም ሆነ በውጭ ያለን ሁሉ አንድነታችንንና ሠላማችንን ልንጠብቅ ይገባል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም