በትግራይ መቀንጨርን ለመከላከል የተጀመረው ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳየ ነው

64
መቐለ ነሐሴ 02 /2011 በትግራይ ክልል በተከዜ ተፋሰስ አካባቢ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት በህጻናት ላይ የሚከሰተውን መቀንጨርን ለመከላከል የተጀመረው ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ ውጤት በማሳየቱ ወደ ሌሎች ወረዳዎች ሊስፋፋ ነው፡፡ በትግራይ ክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኃይለ አስፈሃ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በትግራይና በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው ። በክልሉ በተከዜ ተፋሰስ አካባቢ በሚገኙ 13 ወረዳዎች ላይ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት በህጸናት ላይ የሚከሰተውን መቀንጨር ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እንደታየባቸው ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በተተገበረባቸው ወረዳዎች በህጻናት ላይ የሚደርሰውን የመቀንጨር በሽታ ከ45 ወደ 39 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል። የፕሮጀክቱን ውጤት በማየት ተመሳሳይ ችግር ወደሚታይባቸው 52 ወረዳዎች ይስፋፋል ብለዋል። የክልሉ መንግሥት ለፕሮጀክቱ በጀት 133 ሚሊዮን ብር በጀት ሲመድብ መቆየቱንና ሥራዎቹ ሲሰፉ በጀቱም እየጨመረ እንደሚሔድ አስረድተዋል ። የፌዴራል መንግሥቱም ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ በጀት እንደሚመድብ አስተባባሪው ገልጸው ፣ በፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናትና ሴቶች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱን በማስፋት የመቀንጨር በሽታ አሁን ካለበት 39 በመቶ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ወደ ዜሮ ለማውረድ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ የመቀንጨር በሽታን ለመከላከል በጤና፣በውሃ፣ግብርናና በትምህርት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም