የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ጉዞ ፈጣን አለመሆን በተጠቃሚዎች ላይ መሰላቸት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ጉዞ ፈጣን አለመሆን በተጠቃሚዎች ላይ መሰላቸት ፈጥሯል
ኢዜአ ነሐሴ 2/2011 የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ጉዞ ፈጣን አለመሆን መሰላቸት እንደፈጠረባቸው ተጠቃሚዎች ገለጹ። የአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር መስመር ከለቡ ባቡር ጣቢያ ተነስቶ አዳማ፣ መኢሶ፣ ድሬዳዋን ጨምሮ 19 ጣቢያዎችንና ስድስት ማቆሚያዎች አልፎ ኢትዮጵያንና ጅቡቲን ያገናኛል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከዋጋ፣ ምቾትና ደህንነት አንጻር ከሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ባቡርን ምርጫቸው አድርገዋል። በተለይም ልጆችን ይዘው ለሚጓዙ መንገደኞች ባቡር ደህንነቱ የተጠበቀና ምቾት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁንና ባቡሩ ፈጣን ባለመሆኑ ጊዜያቸውን በጉዞ እንደሚያሳልፉ ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ጅቡቲ ባቡር መስመር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰርካ በሰጡት ምላሽ በአሰራር በኩል ባቡሩ ችግር እንዳሌለበት አንስተው ባቡሩ በሚያልፍባቸው መስመሮች ያሉ ማቋረጫዎችን ተጠንቅቆ ማለፍ ስላለበት በተፈለገው ፍጥነት እየሄደ አይደም ብለዋል። ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን አካባቢውን ምቹ ለማድረግ የሚሰራውን ስራ በማጠናከር ችግሩ በቅርቡ እንደሚፈታም ተናግረዋል። ባቡሩ የሚያልፍባቸው ማቋረጫዎች ምቹ እስኪሆኑ ድረስ በሰዓት መዘግየት የመንገደኞችን መጉላላት ለማስቀረት የአሰራር ማሻሻያዎች ይደረጋሉ ነው ያሉት። በባቡር መስመሩ ማቋረጫ እንስሳት መግባትና የባቡር መስመሩ ብሎን መፈታት ድርጅቱ ስራውን በአግባቡ እንዳያከናውን ችግር እንደሆኑበት ተነግሯል። ባቡሩ ባለፉት ስድስት ወራት 39 ሺህ ተሳፋሪዎችን በማጓጓዝ ከ537 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል። በተመሳሳይ ወቅት 473 የጭነት አገልግሎት በመስጠት ከ19 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችሏል። ታህሳስ 2010 ዓ.ም ስራ የጀመረው የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር አጠቃላይ ከ751 ኪሎሜትር በላይ ርዝመት አለው። የባቡር መስመሩ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ለኢትዮጵያዊያንና ቻይናዊያን አጠቃላይ ለሶስት ሺህ 900 ሰዎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ አመልክቷል። የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡሩ መስመር በቀን አንድ ሺህ ሰው የማጓጓዝ አቅም ሲኖረው አሁን እያጓጓዘ ያለው 500 መሆኑም ተገልጿል።