አክሱም ዩኒቨርሲቲ በግእዝ እና ትግርኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አክሱም ዩኒቨርሲቲ በግእዝ እና ትግርኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ሊሰጥ ነው
አክሱም ሰኔ 6/2010 አክሱም ዩኒቨርሲቲ በግእዝና ትግርኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በሁለቱ ቋንቋዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የስርአተ ትምህርት ቀረጻ ተጠናቋል፡፡ ለስርአተ ትምህርቱ ተጨማሪ ግብአት ለማሰባሰብ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ የቋንቋና የስርአተ ትምህርት ባለሙያዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በዩኒቨርሲቲው ተካሄዷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ በዚሁ ጊዜ ''ዩኒቨርስቲው በተለይም በግእዝ ቋንቋ ማስተማር መጀመሩ በአክሱም ከተማና አካባቢው በግእዝ የተጻፉ ጥንታዊ ቅርሶችን፣ የስነ ህንጻና ቅርጻቅርጾች በማጥናት ለምርምር እንዲውሉ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል'' ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የግእዝ ፍልስፍናና ቋንቋውን በማሳደግ ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል። እንደ ዶክተር ኪሮስ ገለጻ የግእዝ ቋንቋ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ የግእዝ ተናጋሪ ለመፍጠርና የጥንት ስልጣኔ ምስጢር ለማወቅ ያግዛል፡፡ ''በተመሳሳይ የትግርኛ ቋንቋ በመከፈቱ ቋንቋውን ከማሳደግ ባለፈ የኪነ ጥበብ ኢንዲስትሪ ለማሳደግ ያግዛል'' ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የግእዝ ቋንቋ መምህር ካሳ ንጉስ እንዳሉት የትምህርቱ መጀመር የኢትዮጵያ ሀብት የሆነውን የግእዝ ቋንቋ ለማሳደግ ይረዳል፡፡ የግእዘ ቋንቋ አሻራ ያረፋባቸው አብዛኛው ቅርሶችና፣ መጽሓፍት ወደ ሌላው ቋንቋ በመተርጎም ለሀገር ገጽታ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ጨምረው ገልፀዋል፡፡