ቀጥታ፡

በድሬዳዋ በ35 ሚሊዮን ብር የተገነባ የውሃ ተቋም ለአገልግሎት ተዘጋጀ

ድሬዳዋ ኢዜአ ነሐሴ 2  2011  - በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ35 ሚሊዮን ብር ግንባታው የተጠናቀቀው የመጠጥ ውሃ ተቋም ለአገልግሎት መዘጋጀቱን የከተማው ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ተቋሙ የተገነባበት የለገኦዳ ጉኑንፈታ ቀበሌ ነዋሪዎች በበኩላቸው የውሃ ስርጭቱ ፈጥኖ እንዲጀምር ጠይቀዋል ። በጽህፈት ቤቱ "ዋሽ" ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ከበደ ለኢዜአ እንደገለፁት የቀበሌውን ነዋሪዎች ጥያቄ ለመመለስ ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው የውሃ ተቋም ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል ። የውሃ ተቋሙ በሰከንድ 8 ሊትር ውሃ የማመንጨት አቅም ያለው የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ 50 እና 200 ሜትር ኩብ ውሃ የሚይዙ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታ የተካሄደለት መሆኑን ተናግረዋል። ከማጠራቀሚያ ጋኖች ውሀን ስቦ ወደ መኖሪያ መንደሮች ለማድረስ ከ43 ኪሎ ሜትር በላይ የቧንቧ መስመር ዝርጋታ ስራም መከናወኑን ገልፀዋል ። የውሃ ተቋሙን ስራ ለማስጀመር የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የገለፁት አስተባባሪው የውሃ ስርጭቱን አስተማማኝ ለማድረግ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ሦስት የኃይል ማመንጫዎች ተከላ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ተቋሙ በዚህ ወር መጨረሻ ለህብረተሰቡ ውሃ የማሰራጨት ስራውን ይጀምራል። በጽህፈት ቤቱ የፕሮጀክቱ መሀንዲስ አቶ መገርሳ አብዱልማሊክ  በበኩላቸው የውሃ ተቋሙ ለ50 ዓመት አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ነው። የለገኦዳ ቀበሌ ነዋሪና የድሬዳዋ ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ኑሪያ ሃሚዶ የቀበሌው ነዋሪዎች ያለባቸውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጭምር አሳውቀው እንደነበር አስታውሰዋል ። "ከወራጅ ወንዝ ውሃ ለመቅዳት ጀሪካን ተሸክመን ደርሶ መልስ ለሰአታት እንጓዛለን" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ጀነቲ አልይ ናቸው። የለገኦዳ ጤና ጣቢያ አዋላጅ ነርስ ኤሊያስ አህመድ በበኩላቸው ጤና ጣቢያው በውሃ  እጦት ምክንያት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል። ግንባታው የተጠናቀቀው የውሃ ተቋም በአፋጣኝ ስራ እንዲጀምር ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም