ቀጥታ፡

የጅግጅጋ ከተማ ሰላም አምና እና ዘንድሮ

አዲስ አበባ  ኢዜአ ነሃሴ 2  2011 አምና በጅግጅጋ ተከስቶ የነበረው ቀውስና ዕልቂት ዘንድሮ በተመሳሳይ ወቅት በሰላም ክሶናል አሉ የጅግጅጋ ነዋሪዎች። ዛሬ ላይ በህግ ጥላ ስር በሚገኙት የቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በአቶ አብዲ መሐመድ ዑመር አስተዳድር ዘመን በ2010 ዓ.ም ሐምሌ መገባደጃ ቀናት የጅግጅጋና አካባቢው ድባብ አስፈሪ ነበር። በስፍራው የተወለዱትም ሆነ ለዓመታት ለኖሩ ከክልሉ ህዝብ የተለየ ማንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም የሰቆቃ ጊዜ እንደነበር ነዋሪዎች ያስታውሳሉ፣ አንዳንዶቹ ያን አሰቃቂ ጊዜ ማስታወስ ባይፈልጉትም። አቶ አብርሃም ፈቃዱ ላለፉት 20 ዓመታት በጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ሁሉንም ስላሳዘነው የአምናው ድርጊት ማስታወስ ያሳቅቃቸዋል። በሆቴል የንግድ አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩት አቶ አብርሃም አምና በሰቆቃ ቢያልፍላቸውም ስለዘንድሮዋ ጅግጅጋ ድባብ ሰላምነት ነዋሪው ወደ ነበረበት የስራ እንቅስቃሴው መመለሱን ይናገራሉ። ጅግጅጋ ወደ ነበረችበት ሰላም ብትመለስም ግን በወቀቱ ግጭት እንዲፈጠር ሲገፋፉ የነበሩ አመራሮች ዛሬም ከአዲሱ አመራር መዋቅር ስር ስላሉ መንግስት ያጠፉ ግለሰቦችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል። ይህ ካልሆነ ግን በእርሳቸውና በሌላው ነዋሪ ላይ ወደፊት ሌላ ችግር ይፈጠራል የሚል ስጋት ጨርሶ አልጠፋም። ኃይማኖትና ማንነትን ትኩረት ባደረገው በባለፈው ዓመት ጥቃት በጅግጅጋና አካባቢዋ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛዋ ነበረች። የጅግጅጋ ምስራቅ ፀሃይ ኪዳነ ምህረት ካቴድራል አስተዳዳሪ መልአከ ፀሃይ ቀሲስ እዮብ ወንድሙ እንደሚሉት በወቅቱ በነበረው ዘረፋ፣ ቃጠሎና ግድያ እርሳቸው የሚያስተዳድሯት ቤተ ክርስቲያንና ካህናቱ ተጠቂ ነበሩ። 'በድርጊቱ ካህናትና ምዕመናኑ ተገድለዋል፣ አስከሬናቸውም እስከ መቃጠል ደርሷል' የሚሉት አስተዳዳሪው  ዘንድሮ በተፈጠረው ሰላም ብዙ ዓመት የሚፈጅ ስራን በአንድ ዓመት አጠናቀው ቤተ ክርስቲኗ መጠገኗን አብራርተዋል። ቤተ ክርስቲያኗ በጥሩ ሁኔታ ተገንብታ በተቃጠለች ልክ በዓመቱ ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በድምቀት መመረቋን ለአብነት በማውሳት። በክልሉ ለተፈጠረው ሰላም ትልቁን ሚና የተጫወቱትና ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ወደስልጣን ለመጡት ለአቶ ሙስጠፌ መሐመድና ባልደረቦቻችው ቤተ ክርስቲያኗ ሽልማትና ዕውቅና መስጠቷንም ይናገራሉ። በስፍራው ተወልደው ማደጋቸውን የሚናገሩት ቀሲስ እዮብ የሱማሌ ህዝብ ለጥምቀት ሳይቀር በዓሉን ለማየትና ለማድመቅ ባህረ ጥምቀት የሚታደም ሰላማዊ ህዝብ እንደሆነ ገልጸው፤ ችግሩ "የሴራ ፖለቲካ ውጤት ነበር" ባይ ናቸው። ለዚህም ባለፈው ዓመት ለተከሰተው ግጭትም የህዝቡ መሰረታዊ ባህሪ ላለመሆኑ ዛሬ ያለው ሰላም ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያናቱ ዳግም እንዲገነቡና እንዲታደሱ ማድረጉን ይመሰክራሉ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሱማሌ ክልል ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ አባ መልአከ ሠላም ቀሲስ ደረጀ በቀለ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ግጭት በአጠቃላይ አስር አብያተ ክርስቲያናት ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። በክልሉ ጉዳት ከደረሰባቸው አስር አብያተ ክርስቲያናት መካከል አምስቱ እስካሁን መሰራታቸውን ገልጸው፤ የቀሪዎችም ስራ መጀመሩን ተናግረዋል። ሰው በማንነቱ፣ በሃይማኖቱና በብሄሩ ጉዳት እንዳይደርስበት አሁን ያለው ሰላም ከዚህ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት አባ መልአከ ሠላም፣ ቤተ ክርስቲያኗም ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል። የወቅቱ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሐመድ ዑመር ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ በማድረጋቸውም አመስግነው፤ የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ቀሲስ ደረጀ። የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ከሰሞኑ በተደረገው የኦሮሞና ሱማሌ የህዝብ ለህዝብ መድረክ ተገኝተው ለአቶ ሙስጠፌና ባልደረቦቻቸው የክብር ካባ መሸለማቸውን መዘገባችን ይታወሳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም