አዲስ አበባ በሆቴል መኝታ ክፍያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ በሆቴል መኝታ ክፍያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች
ነሃሴ 2/2011 በአዲስ አበባ በባለኮከብ ሆቴሎች ለአንድ ቀን አዳር የሚከፈለው አማካይ ዋጋ 163 ዶላር ከ79 ሳንቲም ሆኖ መመዝገቡን መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የአፍሪካ ፕሬስ ማህበር አስታውቋል። ምጣኔው የተሰላው መደበኛ የሆነውን የአገሪቱን የምንዛሪ ዋጋ ተከትሎ ሲሆን በአገሪቱ ያለውን ግሽበት አላካተተም። ዕለታዊ ምጣኔውን በመከተል ጥናቱን ያከናወነው ኤስ ቲ አር ዶት ኮም የተሰኘ ተቋም የ 12 ወራት ክፍያን መሰረት ማድረጉን አስታውቋል። ገበያው የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረምን ለማዘጋጀት ዕድል ያስገኘ ሲሆን ፎረሙ መስከረም 2012 በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል እንደሚደረግ ተገልጿል። ከሐምሌ 2010 እስከ ሰኔ 2011 ባለው ጊዜ አዲስ አበባ ከፍተኛ የተባለውን የሆቴል ዕለታዊ ክፍያ 163 ዶላር ከ79 ሳንቲም ያስመዘገበች ሲሆን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 11 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል። ከአዲስ አበባ በመቀጠል ተቀራራቢ ገቢ ያስመዘገበችው የጋና ዋና ከተማ አክራ ሰትሆን ለአንድ ቀን አዳር ሆቴሎቿ 160 ዶላር ከ34 ሳንቲም ሲጠይቁ የናይጀሪያዋ ሌጎስ ደግሞ 132 ዶላር ከ 51 ሳንቲም በማስከፈል እንግዶቿን ታሳድራለች። “ አዲስ አበባ ከዓለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲወዳደር አሁንም ከፍተኛ የተባለውን አማካይ ዕለታዊ ክፍያ በመቀበል ጉዞዋን ትቀጥላለች“ በማለት የኤስ ቲ አር ዳይሬክተር ቶማስ ኢማኑኤል ተናግረዋል። “ከተማዋን ተመራጭ ያደረጓት በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፤ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ፣ ስኬታማ አየር መንገድና የአፍሪካ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷ ተፈላጊነቷን አሳድጎታል “ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካዊ ትስስር በመፍጠር ነገሮችን ምቹ ማድረጉ ፍላጎቱን ከፍ እንዲል አድርጎታል።ይህም ሆቴሎቿ ዋጋቸውን እንዲያሳድጉ መተማመን ፈጥሮላቸዋል ይላሉ። “በኢንቨስትመንት በኩል ያለው ጤናማ አፈጻጸም የሆቴል ገበያውን ከፍ ያደረገው ሲሆን በግንባታ ላይ የሚገኙ 22 ሆቴሎችና አራት ሺህ 820 አልጋዎችን በመጠቀም ገበያዋን እንደምታሰፋም እንገምታለን ብለዋል። እኛም አዲስ የሚከፈቱትን ሆቴሎች በመመዘን ገበያው ምን ያሀል እንደሚሰፋ እንከታተላለን“ በማለት ቶማስ ኢማኑኤል ተናግረዋል። ኢማኑኤል ሆቴሎቹ ያላቸውን አፈጻጸምና ዕድገት በተመለከተ መስከረም 2019 በአዲስ አበባ ጥ ቆማ እንደሚሰጡ ይጠበቃል በማለት ዘገባው አሳውቋል። “የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረም አይነት ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸውን ጉባኤዎች ማስተናገድ አዲስ አበባን በሆቴል ክፍያ ከአፍሪካ ውዷ ከተማ አድርጓታል” በማለት የቤንች ኢቨንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማቲው ዌልስ ተናግረዋል። “የእኛ ልዑካን ከፍ ያለ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችን በጥናት በመገምገም እንዲሁም የጉባኤ አዳራሽ ዋጋዎችን በማጥናት አዲስ አበባን ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እንሰራለን “ብለዋል። ቤንች ኤቨንት የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረም አዘጋጅ መሆኑ ይታወቃል። በአዲስ አበባ በሆቴል ዘርፍ በ12 ወራት ብቻ 58 ነጥብ 4 በመቶ የስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በ 6 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለወም ድረ-ገጹ አሳውቋል። በዘርፉ የግብጾቹ ካይሮና ጊዛ 74 ነጥብ 5 በመቶ ስራ በመፍጠር ከአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆኑ የደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን 65 በመቶ እንዲሁም ጋና አክራ 59 በመቶ በማስመዝገብ ከኢትዮጵያ ፊት ተቀምጠዋል።