ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች 142 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አገኘች

አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2011 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች 142 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ። በኢትዮጵያ የቻናይና ኢምባሲ ለሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች፣ ለአገር ውሰጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ለቡ መነሻ ጣቢያንና በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የቻይና ኢንቨስተሮችን የስራ እንቅስቃሴ አስጎብኝቷል። የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሃና አርያስላሴ  ወደ ኢትዮጵያ ከሚመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመን 85 በመቶ ድርሻ የሚይዘው የማምረቻው ዘርፍ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ ባለፉት ዓመታት እየቀነሰ ቢመጣም ከማምረቻው ዘረፍ የሚገኘው ገቢ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢንዱስትሪ ፓርክ 142 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን በመጠቆም ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል። የጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶችና ሌሎች ምርቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ተገልጿል። ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ቀመጡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የቻይና ባለሃብቶች ተሳትፎ  ጉልህ መሆኑንም ጠቁመዋል። በሁለቱ አገራት መካካል ባለው የጠበቀ ግንኙነት የተገኘ ውጤት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሯ በ2018 በጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ ከቬትናም ቀጥላ ሁለተኛ መሆን አስችሏታል ብለዋል። በአዲስ አበባ የቻይና አምባሳደር ታን ጄይን ለኢዜአ እንደተናገሩት የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው ይቀጥላሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያወሰቱ አምባሳደር ታን በቀጣይም በርካታ የቻይና ኢንቨስተሮች ኢንቨስት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ ካላት ህዝብና እያሳየች ካለው የኢኮኖሚ እድገት እንቅስቃሴ አንጻር ለምስራቅ አፍሪካ የልማት ትስስር ትልቅ ድርሻ ይኖራታልም ነው ያሉት። የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ሲያደርጉ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን በርካታ አማራጮች አይቻለሁ ያሉት አምባሳደሩ በቀጣይም የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ይጠናከራል ብለዋል። በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሰንሻይን፣ ኪንግደምና አንቴክስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጎብኝተዋል። በ70 ሺህ ሜትር ስኩር ላይ ያረፈው ሰንሻይን ኢትዮፕጵያ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሁለት ምዕራፍ 980 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት ለማድርግ ያቀደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ መዋለ ነዋይ ስራ ላይ አውሏል። በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን አጠቃላይ በምዕራፍ አንድና ሁለት ለ20 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። አሁን ላይ በዓመት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ውጤቶችን ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚልክ ሲሆን ምዕራፍ አንድ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል ነው የተባለው:: ኪንክደም የተባለው ጨርቃጨርቅ አምራች ኮባንያም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በራሱ ሼድ አልምቶ ወደ ስራ ለመግባት እየሰራ ይገኛል። በሶስት ምዕራፍ ወደ ስራ የሚገባው ካምፓኒው በመጀመሪያው ምዕራፍ በ70 ሚሊዮን ዶላር እያስገነባ ያለውን የኢንዱስትሪ ሼድ በማጠናቀቅ ማሽነሪዎችን በመትከል ላይ ሲሆን በመጪው ጥቅምት ወር ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በመጀመሪያው ምዕራፍ በዓመት ከ5 ሺህ ቶን የላይነን ጨርቅ በማምረት ሙሉ ለሙሉ ወደ ውጭ በመላክ 45 ሚሊዮን ዶላር ላማስገባት እቅድ ይዟል። በአምስት አመት ውስጥ የ150 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድርግ በማቀድ ከ2 ዓመት በፊት ስራ የጀመረው አንቴክ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት መዋለ ነዋይ በማፍሰስ በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እየሰራ ይገኛል። በኢትዮጵያ መንግስት የተገነባው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 148 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል። በውስጡ 19 የማምረቻ ሼዶች ያሉ ሲሆን ዋነኛ ትኩረቱን ጨርቃጨርቅ ምርት ላይ በማድረግ ለ12 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም