የምዕራብ ጎንደር ነዋሪዎች ህገ ወጥ የደን ምንጠራን ለመከላከልና ችግኞችን ለመንከባከብ እንደሚሰሩ ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ ጎንደር ነዋሪዎች ህገ ወጥ የደን ምንጠራን ለመከላከልና ችግኞችን ለመንከባከብ እንደሚሰሩ ገለፁ
ጎንደር ነሀሴ 1 / 2011የምዕራብ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች የተተከሉትን ችግኞች ከመንከባከብ ባሻገር ህገ ወጥ የደን ምንጠራ የሚያካሔዱ ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ገለፁ ። በዚህ ዓመት የተተከሉትንና በዞኑ ያለውን የተፈጥሮ ደን በባለቤትነት ስሜት መንከባከብ የህልውና ጉዳይ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል ። የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ በበኩሉ የተፈጥሮ ደን ሲጨፈጭፉ በሚገኙ ግለሰቦች ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል። በመተማ ወረዳ ወዲ ገምዞ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር በለጠ ሽባባው እንደተናገሩት ከዚህ በፊት የእርሻ ቦታን ለማስፋፋት በሚል የተፈጥሮ ደኖችን ያለአግባብ ሲጨፈጭፉ እንደነበር አስታውሰዋል። በአካባቢያቸው የሚኖሩ አርሶ አደሮችም በተመሳሳይ መልኩ የእርሻ ማሳን ለማስፋፋት ደኖችን ሲጨፈጭፉ ማንም ጠያቂ እንዳልነበረ አስረድተዋል ። ”በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮ ደኖች ከጠፉ የእርሻ ማሳዬ ሰብል ማብቀልና ማምረት እንደማይችል ተረድቻለሁ” ያሉት አርሶ አደሩ በቀበሌያቸው በዚህ ዓመት የተተከሉትን ችግኞች ጨምሮ ነባር ደኖችን እንደሚጠብቁ ቃል ገብተዋል። በዞኑ ቋራ ወረዳ ተወልደው ያደጉትና የ62 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት አቶ ቢራራ ካሳው በበኩላቸው ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ወቅቱን የጠበቀና የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት እንደነበር ያስታውሳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የዝናብ ስርጭቱ እየቀነሰና ወቅቱን ባለመጠበቁ እየተፈጠረ ያለው ስጋት በደኖች መመናመን ምክንያት መሆኑን ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ለደኖች አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል። “ በየአካባቢያችን ያሉ ደኖችን መጠበቅ በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው” ያሉት ደግሞ የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደር ግዛቸው ታደሰ ናቸው፡፡ በደኖች ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለመከላከል የአካባቢያቸውን ማህብረሰብ በማስተባበር ለማስቆምና ከአቅም በላይ የሆነውን ለሚመለከተው አካል አጋልጦ በመስጠት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናገረዋል። የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌትነት በልይሁን እንደተናገሩት በዞኑ 266 ሺህ 570 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የአልጣሽና 18ሺህ 691 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የጎደቤ ብሔራዊ ፓርኮች ይገኛሉ። በዞኑ 19 ሺህ ሔክታር መሬት ስፋት ያለው የማህበረ ስላሴ አንድነት ገዳም ሳይጨምር 455 ሺህ ሔክታር መሬት የተፈጥሮ ደን እንደሚገኝ አመልክተዋል። "ነባር የተፈጥሮ ደን ሀብቶችንና አሁን የሚተከሉ ችግኞችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ ርብርብ ይካሄዳል" ብለዋል። በወል መሬት ላይ ያሉ ደኖችን በመለየት በህብረተሰቡና በአሳታፊ የደን አስተዳደር ውስጥ በማካተት ራሱን የቻለ ጥበቃ እንዲኖራቸው ለማድረግ እየተሰራ ሲሆን በአጥፊ ግለሰቦች ላይ የማያዳግም እርምጃ የሚወሰድበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑንም ተናግረዋል። በዞኑ ስር በሚገኙ አራት ወረዳዎች በሁሉም ቀበሌዎች ህገ-ወጥ የደን ጭፍጨፋን የሚከላከል ግብረ-ኃይል በየደረጃው በማቋቋም ዘላቂነት ያለው የመከላከል ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን በዘንድሮው የክረምት ወራት 400 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እስከ አሁን ድረስ 480 ሺህ ችግኞችን በመትከል ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል። በምዕራበ ጎንደር ዞን ያለው የደን ሽፋን 31 በመቶ ሲሆን ለከሰልና የእርሻ ቦታን ለማስፋፋት በሚካሄድ ህገ ወጥ ድርጊት በየዓመቱ ከ40 ሄክታር በላይ ደን እንደሚወድም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡