የማሾ ሰብል ብናመርትም ገበያ በማጣት ለኪሳራ እየተዳረግን ነው---አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የማሾ ሰብል ብናመርትም ገበያ በማጣት ለኪሳራ እየተዳረግን ነው---አርሶ አደሮች
ጎንደር ነሀሴ 2 / 2011 በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆነውን የማሾ ሰብል ብናመርትም ገበያ በማጣት ለኪሳራ እየተዳረግን ነው ሲሉ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የኪንፋዝ በገላ ወረዳ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን ገለጹ፡ በጎንደር ከተማ የሚገኘው ጸሐይ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን በበኩሉ የአምራች አርሶ አደሮችን የገበያ ችግር ለመፍታት በተያዘው በጀት ዓመት ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ የማሾ ምርት ለመግዛት ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በወረዳው የስላሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እሸቴ ፈረደ እንዳሉት የማሾ ሰብል ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚና በአጭር ጊዜ የሚደርስ መሆኑን በመረዳት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ተመካክረው ቢያመርቱም የገበያ ችግር ገጥሟቸዋል። “ባለፈው ዓመት በግማሽ ሄክታር ካለማሁት የማሾ ሰብል 12 ኩንታል ምርት ባገኝም በገበያ እጦት ምክንያት ግማሹን ለአካባቢው ሰው በርካሽ ዋጋ በመሸጥ ቀሪውን ለቤተሰብ ቀለብ አውየዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው ምርታቸውን አዲስ አበባ ድረስ በማጓጓዝ ለገበያ ለማቅረብ የተገደዱበት ሁኔታ እንደነበር የገለጹት ሌላው የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ድረስ ካሳ ናቸው፡፡ ባላፈው ዓመት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አዲስ አበባ ድረስ የላኩት የማሾ ምርት መኪና ተገልብጦ እህሉ ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ለኪሳራ መዳረጋቸውን አስታውሰዋል። “የማሾ ምርት በዓለም ገበያ ተፈላጊና ዋጋውም ከሌሎች ሰብሎች የተሻለ ነው” ያሉት አርሶ አደር ቢሰጥ መኳንንት በበኩላቸው በገበያ እጦት አምና በግማሽ ሄክታር ያመረቱትን 10 ኩንታል ምርት ተረካቢ ማጣታቸውን ተናግረዋል። የኪንፋዝ በገላ ወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዛናው ታምራት በበኩላቸው አርሶ አደሮቹ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነው ችግሩን ለመፍታት ከፀሐይ የገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ጋር በመተባበር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በወረዳው አምና ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የማሾ ማምረት ሥራ በ18 የገጠር ቀበሌዎች የተለዩ 675 አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። “በማሾ ከለማው 335 ሄክታር መሬትም 3ሺህ 231 ኩንታል ምርት ማምረት ተችሏል” ብለዋል፡፡ በ2011/12 የምርት ዘመን 403 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 450 ሄክታር በማሾ ሰብል እየለማ መሆኑን ጠቁመው በምርት ዘመኑ 5ሺህ ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል። የማሾ ሰብል ለዝናብ አጠር አካባቢዎች እጅግ ተስማሚና በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚደርስ በመሆኑ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። “ሰብሉ በዓለም ገበያ ተፈላጊ ከሆኑ የግብርና ምርቶች አንዱ በመሆኑ አንድ ኩንታል የማሾ ምርት በወቅቱ የገበያ ዋጋ 2 ሺህ 500 ብር እየተሸጠ ይገኛል” ብለዋል፡፡ የፀሐይ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ በበኩላቸው አርሶ አደሮች የገጠማቸውን የገበያ ችግር ለመፍታት ዩኒየኑ በተያዘው የምርት ዘመን 10 ሺህ ኩንታል ማሾ ለመረከብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ አምና ዩኒየኑ ከምዕራብና ምስራቅ በለሳ ወረዳዎች 3ሺህ ኩንታል የማሾ ምርት በመረከብ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ለውጪ ገበያ እንዲቀርብ ማድረጉንም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት በማሾ ሰብል ከለማው 3ሺህ 531 ሄክታር መሬት 45ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ከዞኑ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በተያዘው የምርት ዘመን 5ሺህ ሄክታር መሬት በማሾ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን 65 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።