የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን ከመልካም አስተዳደር ችግር ነጻ አድርገው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን ከመልካም አስተዳደር ችግር ነጻ አድርገው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል
አዲስ አበባ ነሀሴ 1/2011 የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን ከመልካም አስተዳደር ችግር ነጻ አድርገው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ተገለጸ። የኃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን ከመልካም አሰተዳደር ችግር ነጻ አድርገው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ተገለጸ። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኃይማኖት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ሁኔታዎችን የተመለከተ ውይይት እያካሄዱ ነው። ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ውይይት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርሰቲያናት ህብርት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስና የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል። በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስቴርን ወክለው ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ሓለፎም በላይ በእምነትና በኃይማኖት ተቋማት ወስጥ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አየተስተዋሉ ይገኛሉ ብለዋል። ‘’የኃይማኖት ተቋማት የመልካም አስተዳደር ነባራዊ ሁኔታዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች’’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ የተቋማቱ የአመራርና አሰተዳደር ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮቹ ዋነኞቹ መሆኑንም ገልጸዋል። በተቋማቱ የተሟላ ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖር፣ ተቋማቱ ዴሞክራሲያዊና ዘመናዊ የአስተዳደር ዘይቤ አለመከተል እንዲሁም ከሌሎች የኃይማኖት ተቋማት ጋር ያለ የተዛባ ግንኙነትም ሌላው ችግር ነው ብለዋል። በተጨማሪም የአስተዳደር ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ አለመሆን፣ የአደረጃጀት ተደራሽነትና ተሰሚነት አለመኖር፣ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮዎችን ቀላቅሎ መመልከትና በብሔር፣ በአካባቢና በትውውቅ መሰባሰብና መጠቃቀም በስፋት እየተስተዋሉ ይገኛሉ ነው ያሉት። የኃይማኖት አባቶቹ በበኩላቸው ችግሩ ሰፋ በሎ አየተስተዋለ በመሆኑ ተጽዕኖው አሁን በአገሪቷ ለሚታዩ የተለያዩ ችግሮች እንደምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችልም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጸድቁ አብዶ የመልካም አስተዳደር ችግሮቹ እንደየ ቤተ እምነቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ችግሩ ግን ሰፊ ነው ብለዋል። ‘’አንዳንድ ጊዜ የአንድ ሰው አመራር ነው ያለው፤ የተመሳሳይ ቡድኖች፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የአንድ ቤተሰብ ይሆናል ቤተክርስትያኑ’’ ያሉት ፓስተር ጻድቁ፤ ይህ ደግሞ ተቋማቱ ሚዛናዊ አገልግሎት እንዳይስጡ እያደረገ ነው ብለዋል። የእምነት መሪነት ቦታን ያለመልቀቅ፣ ቢለቁም ለቅርብ ሰው የማስረከብና ወጣቶችን ማራቅም ተጨማሪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲሆኑ ጉዳዩ ካልተፈታ ቸግሩ ለአገርም ይተርፋል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ቤተ እምነቶች በኃላፊነትና በተጣያቂነት ስሜት ለዓለማዊ አስታዳደራዊ ስራዎች ምሳሌያዊ ተግባር በማከናወን አርዓያ መሆን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ሌላው ከኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል የተወከሉት ፓስተር ዳንኤል ዘውዱም እንዲሁ የመልካም አስታዳደር ችግር ከመንግስታዊ ተቋማት ባልተናነሰ መልኩ በቤተክርስቲያንም እየተስተዋለ ይገኛል ይላሉ። ‘’በቤተ እምነት ውስጥ እውነተኛና ትክክለኛ ስራ ካልተሰራ በዓለማዊ ተቋማት ደግሞ ችግሩ ይጎላል’’ ያሉት ፓስተር ዳንኤል፤ የኃይማኖት ተቋማት የደቀ መዝሙርሚና ሊጫወቱ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። በተለይ የቤተ እምነት መሪዎች የፈጣሪያቸውን አርዓያነት በመከተል በዙሪያቸው ያሉትን ምዕመናን በትክክለኛው መንግድ ማገልገል እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማተ ጉባኤ ጠቅላይ ፀሓፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋየ ታደለ በበኩላቸው ጉባኤው በኃይማኖት ተቋማት እየተስተዋለ የሚገኘውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት እየሰራ ነው ብለዋል። በተለይ ደግሞ ተቋማቱ ራሳቸውን ከዚህ ችግር ነጻ በማድረግ በዜጎች ላይ በስፋት እየተሰተዋለ ያለውን ግብረ ገብነት ማጣት ችግሮችን ለመቀነስ ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት። ከሁሉም በላይ ቤተ እምነቶች ብዝሃነትን፣ አንድነትንና ሰላምን በመስበክ እየተሸረሸሩ ያሉ ምግበራዊ እሴችን ለመመለስ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል። የውይይት መድረኩ ለቀጣይ ሁለት ቀናት በተመሳሳይ ጉዳይ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።