በትግራይ ክልል የአሸንዳ በዓል ሳይበረዝና ሳይከለስ መከበር አለበት---እናቶች

96
መቀለ ነሐሴ 01/ 2011 በትግራይ በተለያዩ አከባቢዎች በልጃገረዶች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል ጥንታዊ ባህሉን ጠብቆ መከበር እንዳለበት እናቶች አሳሰቡ። በተለይ ለበዓሉ ድምቀትና ይዘት መጠበቅ ከልጃገረዶቹ ኃላፊነት አንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ልጃገረዶቹ በዓሉን ለባህላቸውና ለቋንቋቸው ማደግ ፣ፍቅራቸውን ለማጠናከርና ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ ሊያውሉት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። በዓሉ በዓለም ቅርስነት የሚመዘገበው ጥንታዊ መሠረቱን ሳይለቅ በመሆኑ ልጃገረዶች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የአክሱም ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አስቴር ተኽላይ በዓሉ ከነሐሴ 24 ቀን ጀምሮ በከተማዋና አካባቢዋ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ‘’ዓይኒ ዋሪ’’ በሚል ስያሜ እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉን ልጃገረዶች በባህላዊ አልባሳት ተውበውና በጌጣጌጦች ደምቀው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ሳይቀይር ለዘመናት ሲያከብሩት እንደኖሩም አስታውሰዋል። አሁንም ሳይበረዝና ሳይከለስ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ከልጃገረዶቹ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል። የበዓሉ ታዳሚ ልጃገረዶች የዓይኒ ዋሪ/አሸንዳ/በዓል ፍቅርና አንድነትን የሚያላብስ እንጂ፤ ዘርና ብሄር እንደማይለይ በተግባር ሊያስተምሩ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። ልጃገረዶች ባህላዊ የጥበብ ውጤት የሆኑ አልባሳትን ለብሰው ለታዳሚዎች ለማስተዋወቅ የሚያደርጉት ጥረት የሚያበረታታ ነው ያሉት ደግሞ የመቐለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ከበቡ ገብረኪዳን ናቸው። ልጃገረዶቹ በተፈጥሮ የታደሉትን ፀጉር በባህላዊ የሹርባ አሰራር አምረውና ደምቀው እንዲወጡም አሳስበዋል። የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ወክለው የዓዲግራት ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትበርህ ተኽላይ በበኩላቸው ልጃገረዶች በበዓሉ የተሰጣቸውን ነፃነት በመጠቀም ጥንታዊ ታሪካቸውንና እሴቶቻቸውን ለታዳሚዎች እንዲያስተዋውቁ አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል። ልጃገረዶች በዓሉን ከማክበር ባለፈ በክልሉ የሚገኙ ተፈጥራዊና ሰው ሰራሽ መስህቦችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች ማስተዋወቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። በዓሉ በትግራይ በተለያዩ አካባቢዎች ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ በድምቀት ይከበራል። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በዓሉን በድምቀት እንዲከበርና በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም