የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ ሐዋሪያቶች የራስን ጥቅም ከማስቀደም መቆጠብ አለባቸው - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ

ነሀሴ 1/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ሐዋርያቶች ከቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውጪ የራስን ስምና ጥቅም ከማስቀደም መቆጠብ እንዳለባቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አሳሰቡ። ለራስ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ምንጭ እየሆነ መምጣቱ ተጠቁሟል። የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ የመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚመክር መድረክ ትናንት ውይይት አዘጋጅቷል። በዚሁ ወቅት የቤተ ክርሲቲያኗ ርዕስ ልቃነ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እንዳሉት፤ አገልጋዮች ከወቀሳና ከመከሰስ ለመዳን መንፈሳዊ አገልግሎት ስርዓቱን ጠብቀው መፈጸም አለባቸው። ቤተ ክርስቲያኗ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና አገልግሎቶችን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል ህግ፣ ደንብና መመሪያ አውጥታ እየተገበረች ትገኛለች። ነገር ግን የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ ህግ በሚጥሱ አገልጋዮች በጎ ተግባራት እየጠፉ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጉድለቶች እያስከተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል። የቤተ ክርስቲያን ሃላፊዎች የፈጣሪን ትዕዛዝ በመጠበቅ የራሳቸውን ጥቅም ከማስቀደም መቆጠብ እንዳለባቸው ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። ምዕመናኑ በህግና በስነ-ምግባር ታንጸው እንደዲኖሩ ህጻናት ከክፉ ተግባር ተቆጥበው እንዲያድጉ ሃላፊዎቹ በትምህርትና በተግሳጽ ሃይማኖታዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የቀደሙ አባቶችን በስነ-ምግባራቸው አርአያ ሆነው ያቆይዋትን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ስርዓቱን ጠብቀው እንዲፈጸሙ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል። የሃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሐይማኖት ተቋማት የመልካም አስተዳደር እጦት ፈታኝ ችግር ሆኗል። በሰራተኛ ስምሪት፣ በአድሎ፣ ተገቢ ባልሆነ የጥቅም ትስስር፣ በሙስናና በፋይናንስ አስተዳደርና መሰል ችግሮች እንደሚታዩ ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም የነበራትን ተደማጭነት እንድትመልስ በውስጥ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በትኩረት መስራት አለበት። የሃይማኖት ተቋማት ሃላፊዎችም ውስጣቸው ያለውን ችግር በመወያየት በመፍታት አርአያነት ያለው ተግባር መፈጸም ይጠበቅባቸዋል። የዛሬው መድረክም ተቋማቱ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ለተከታታይ አራት ቀናት በሁሉም የሃይማኖት ተቋማት በየተራ የሚካሄድ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም