ቀጥታ፡

ማህበሩ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለ120 አካል ጉዳተኞችና ጧሪ የሌላቸው ወገኖች ቤት ሊገነባ ነው

ጎንደር ነሐሴ 1 / 2011 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለ120 ወገኖች ቤት እንደሚገነባ የማህበሩ ጎንደር ቅርንጫፍ አስታወቀ። በግጭቱ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የማህበሩ የጎንደር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቤቶቹ ተሰርተው የሚሰጡት በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በግጭቱ ለተፈናቀሉና ቤት ላልነበራቸው ወገኖች ነው፡፡ የቤቶቹን ግንባታ የሚካሄደው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ ወረዳና በምዕራብ ጎንደር ዞን ደግሞ በሽንፋና ነጋዴ ባህር በተባሉ አካባቢዎች እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ማህበሩ ለመኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የግንባታ ቦታ መረጣ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ የግጭቱ ሰለባ ለሆኑት ወገኖች ለእያንዳንዳቸው 45 የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሦስት ካርቶን ሚስማር በማቅረብና የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማስተባበር ቤቶቹን ይገነባል ብለዋል። በቤት ግንባታ ወቅት ለእንጨትና ለጭቃ ምርጊት በነፍስ ወከፍ ቤት ግንባታ 16ሺህ ብር  መለገሱን ተናግረዋል፡፡ ግንባታቸውን እስከ መስከረም 2012 በማጠናቀቅም የጉዳቱ ሰለባዎች የቤት ባለቤት እንደሚያደርግ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ ማህበሩ ባለፉት ሰባት ወራት በዞኖቹ በግጭቱ ወቅት ተፈናቅለው በመጠለያ ለነበሩ ወገኖች ግምቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ አልባሳት፣ምግብ ነክና የቤት ቁሳቁሰ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የጭልጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አቡሃይ ጌትነት በወረዳው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት 2ሺህ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ባቀረበው 73ሺ የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሚስማር 1ሺ 567 መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ከ7ሺህ በላይ አባወራዎችና ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በግጭት ተፈናቅለው  በ11 ጊዜያዊ መጠለያዎች የቆዩ ከ47ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ባለፈው ወር ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። ጊዜያዊ መጠለያዎቹም ተዘግተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም