የቡና ምርትን በዓለም በስፋት ለማስተዋወቅ እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትኩረት ማድርግ ይገባል ተባለ

አዲስ  አበባ ሐምሌ 29/2011 የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ላይ በስፋት እንድታወቅ ለማድረግ እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትኩረት ማድርግ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቡና ላኪዎች ገለጹ። ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው የቡና ምርት 70 በመቶ የሚሆነው ያልታጠበ ጥሬ ቡና መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለውጭ ገበያ ከቀረበው 30 በመቶው ብቻ የታጠበ ቡና ሲሆን እሴት ጨምሮ በማቅረብም ብዙ አልተሰራበትም ተብሏል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኢትዮያ ቡና ላኪዎች ማህበርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የምክክር መድረክ አካሂዷል። የቡና ላኪዎች በዚሁ ጊዜ እንዳሉትም የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ታዋቂ ስም እንዲኖረውና ጥሩ ገቢ እንዲኖረው ለማስቻል እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትኩረት ማድርግ ያስፈልጋል። የቀርጫንሼ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር  ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስራኤል ደገፋ እንደሚሉት፣ የሌሎች ቡና አብቃይ አገራት የራሳቸው የሆነ አገራዊ መለያ ወይም ''ብራንድ'' አላቸው በእሴት ጭመራ ላይም እየሰሩ ነው። ኢትዮያን በዓለም በጣም ቆንጆ ጣዕም ካላቸው ቡና አብቃይ አገራት አንዷ ብትሆንም እሴት ጨምሮ በመላክና ብራንድ ፈጥሮ በማስተዋወቅ አልተሰራበትም። የሞዬ ኮፌ ሮስቲንግ ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ አሃዱ ውብሸትም የኢትዮጵያን ቡና በአለም ላይ ለማስተዋወቅ እሴት የተጨመረበት ብራንድ ያለው ምርት መላክ ያስፈልጋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ቡና በይርጋ ጨፌና፣ ሲዳማ መለያ የሚላከውም በጥሬ ምርትነት ብቻ ስለሚላል የልዩ ንግድ ስያሜው ብዙም አልታወቀም ብለዋል። ይህም የአለም የቡና ዋጋ ከፍ ሲልም ይሁን ሲወርድ በተመሳሳይ የኢትዮያም በዚያም ልክ ይወርዳል ይጨምራል ያሉት አቶ አሃዱ፤ ነገር ግን  የቡና ዋጋ ሲቀንስ እንደ ''እስታርባግስ'' ያሉ የቡና መለያ ባለቤት ትርፋማ ይሆናሉ። ምክንያቱም የመጨረሻው የምርቱ ሻጭ መለያውን በመግዛት ይጠቀማል ስለዚህም የኢትጵያ ቡና ልዩ ሆኖ አንዲወጣ በእሴት መጨመር ላይ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። የጌዴኦ ዞን የቡና አምራችና ላኪ አርሶ አደር የሆኑት አቶ ጸጋዬ ጤቄቦ፣ በበኩላቸው የቡና ተክል ያረጀ ከሆነ ምርታማነትም ጥራትም የሌለው ሊሆን ስለሚችል በአዲስ የቡና ተክል ላይ ትኩረት ማድርጋቸውን ተናግረዋል። በ2011 በጀት ዓመት 300 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር። ሆኖም በዓለም የቡና ዋጋ ማሽቆልቆል ሳቢያ 230 ሺህ ቶን ቡና ብቻ ለውጭ ገበያ በማቅረብ 763 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ማግኘት ተችሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም