የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የ2 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ የ2 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2011 የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮ-ጅቡቲ መንገድ ልማት ፕሮግራም አካል ለሆነው የአዳማ አዋሽ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ የ2 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። የድጋፍ ስምምነቱን የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከባንኩ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዶክተር አብዱል ካማራ ጋር ተፈራርመዋል። ፕሮጀክቱ በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚከናወን ሲሆን 126 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው። ድጋፉ የመጀመሪያውን ምዕራፍ 60 ኪሎ ሜትር ግንባታ ለማካሄድ እንደሆነ ተገልጿል። ከአዳማ እስከ መልካ ጂሎ የሚካሄደው ይሄው የፍጥነት መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ በመንገድና ንግድ ዘርፍ ያለውን ቀጣናዊ ትብብር እንደሚያጠናክርም ይታመናል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤መንግሥት በመንገድ ልማት መርሃ ግብር የአገር ውስጥና ቀጣናዊ ትስስርን እውን ለማድረግ መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንት እያካሄደ ነው። በዚህ ሂደት የአፍሪካ ልማት ባንክ የሚመሰገን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል። የኢትዮ ጂቡቲ መስመርን በመንገድ መሰረተ ልማት ማልማት አገሪቷ ያላትን የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ በመሆኑ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቅሰዋል። በተለይም በቀጣናው የሚደረጉ የንግድ ግንኙነቶች፣ የተሻለ የመንገድ ትስስር እንዲኖር በማድረግና የመንገድ ደህንነትን ከማረጋገጥ ባለፈም የመኪና ወጪና ጊዜ የሚቆጥብ ነው ሲሉም አክለዋል። ቀጣይ የፕሮጀክቱ የግንባታ ምዕራፎች በመንግሥትና በግል ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክት የሚደገፍም ይሆናል። እንደ ሚኒስተሩ ገለፃ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ተጓዞች፣ ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለአከባቢው ማህበረሰብ የስራ ዕድል ይፈጥራል፤ የትምህርትና የጤና አገልግሎትም እንዲሻሻል የራሱን አወንታዊ ሚና ይጫወታል። ባንኩ የሞምባሳ-ናይሮቢ- አዲስ አበባ መንገድና የኢትዮ ኬንያ የኃይል ትስስር መርሃ ግብሮችን መደገፉ በቀጣናው በአገራት መካከል ትስስር ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑንም ገልጸዋል። በአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ኃላፊ ዶክተር አብዱል ካማራ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በኃይል ልማት፣ በመንገድ፣ በውሃና ሳኒቴሽን፣ በግርናና መሰረታዊ አገልግሎቶች ዙሪያ ባንኩ ድጋፍ ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል። በተለይም በመንገድ ዝርጋታ ሰፊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው ከሞያሌ- ሀዋሳ፣ የሞጆ-ዝዋይ የፍጥነት መንገድ፣ በደሌ - መቱ እንዲሁም ሶዶ-ሳውላ መንገድ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል። የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ በግብርና ኢንዱስትሪ ዙርያ እየተከናወኑ ላሉ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፉ ማድረጉም ይታወሳል። በቀጣይም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሃላፊው አረጋግጠዋል።