ቀጥታ፡

የወርቅ ማዕድን ጠቋሚ መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተከፈተ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 29/2011በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የወርቅ ማዕድን ጠቋሚ መሳሪያ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ተከፈተ። በአምስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተቋቋመው ፋብሪካ ለ25 ሰዎች የስራ ዕድል አስገኝቷል ተብሏል። ፋብሪካው የተቋቋመው ማይንላብ ኤሌክትሮኒክስ እና አል ሂላሊ የማዕድን አማካሪ ቡድን በተሰኙ የአውስትራሊያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ድርጅቶች ጥምረት ነው። የማይንላብ ኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ፓርክ ፕሬዚዳንት ፒተር ቻርልስዎርዝ እንዳሉት ቴክኖሎጂው ከደለል አፈር ጋር የተቀላቀለ ወርቅና ብረትን በቀላሉ ያሳያል። ውጤታማነቱም በሱዳን፣ በናይጄሪያ፣ በሞሪታኒያና ሌሎችም አገራት መረጋገጡን ተናግረዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ጠቋሚ መሳሪያው ከመሬት በታች እስከ አንድ ሜትር ጥልቀት ያለን የወርቅ ክምችት በቀላሉ ያሳያል። አጠቃቀሙ ቀላል በመሆኑ ለአምራቾችም ሆነ ለአገሪቱ የወርቅና የብረት ማዕድናት ቁፋሮ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ''ዋና ዓላማችን በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በቴክኖሎጂው በመጠቀም ጊዜና ጉልበታቸውን ቆጥበው ውጤታማ እንዲሆኑ ማድረግ ነው'' ብለዋል። የአል ሂላሊ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር አምጌድ ኢል ራሺድ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው በአንድ አካባቢ ያለን የወርቅና የብረት ማዕድን መጠን አስቀድሞ እንደሚለይና በቁፋሮ ወቅት ማዕድናት በበካይ ንጥረ ነገሮች እንዳይበከሉ እንደሚረዳ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ነዳጅና ባዮ-ፊውል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ በአገሪቱ እየቀነሰ ለመጣው የወርቅ ምርት ዋነኛው ምክንያት በባህላዊ መንገድ የሚካሄደው ቁፋሮ መሆኑን ተናግረዋል። ወጣቶችን በማደራጀትና በሚመረተው ጠቋሚ መሳሪያ እንዲሰሩ በማድረግ የአገሪቱን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚቻል ነው ያብራሩት። የወርቅ ክምችት ያለበትን ቦታ በአግባቡ ለመለየትና ከሚታወቁት ቦታዎች በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ፍለጋ ለማካሄድ እንደሚረዳም ገልጸዋል። የወርቅ ማዕድን የተገኘበት አካባቢ ጥበቃ እንዲደረግለት፣ ማዕድኑ ከወጣ በኋላም ወደ ህጋዊ ገበያ እንዲገባ ለማድረግ እንደሚያስችልም አቶ ሙሉጌታ አክለዋል። ''የአምራቾችን የቴክኖሎጂና የገበያ ተጠቃሚነት በማስጠበቅና ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል እያሽቆለቆለ ያለውን የወርቅ ምርት ማሳደግ ያስችላል'' ብለዋል። በዘርፉ ተደራጅተው የሚሰሩ ቴክኖሎጂውን መጠቀም እንዲችሉ ኮርፖሬሽኑ ለባለሙያዎች የአሰልጣኝነት ስልጠና የመስጠትና ከቴክኖሎጂው ባለቤቶች ጋር የማገናኘት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የመግዛት አቅም ለሌላቸው በኮርፖሬሽኑ በኩል በማቅረብ መጠነኛ የአገልግሎት ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረግ ይቻላልም ነው ያሉት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም