"ጾመ-ፍልሰታ ለሕዝብ ሰላም፣ ለአገር ልማትና አንድነት ወደ ፈጣሪ የምንጮህበት ሊሆን ይገባል" - ቅዱስ ፓትርያርኩ

አዲስ  አበባ ሐምሌ 29/2011  ህዝበ-ክርስቲያኑ የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ ፍልሰታን በሚጾምበት ወቅት ለሕዝብ ሰላም፣ ለአገር ልማትና አንድነት ፈጣሪን አጥብቆ በመማጸን ሊሆን ይገባል አሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ2011 ዓም ጾመ-ፍልሰታን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ጾሙ የቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰታን በማሰብ፣ በይቅርታ፣ በምሕረት፣ በጸሎት፣ በአምልኮት፣ በስግደት፣ ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል የእምነቱ ተከታዮች ከፈጣሪ ለመገናኘት የሚጾሙት ነው ብለዋል። ስለዚህም ጾሙን "ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ሕፃን፣ አዋቂ ሳይባል ሁሉም እግዚአብሔርንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በመሻት ፍቅርንና መታዘዝን፣ ሰላምንና አንድነትን እንደሸማ በመጎናጸፍ ሁሉም ሊጾመው ይገባል" በማለት ጥሪ አቅርበዋል። ጾሙ የሕዝቡ ሠላም፣ የአገር ልማትና አንድነት፣ እስከ ዘለቄታው እንዲጠበቅ፣ ፍትሕና እኩልነት፣ ይቅርታና ፍቅር በኢትዮጵያ እንዲነግስ አጥብቀን ወደ ፈጣሪ የምንጮህበት ነው ሲሉም ተናግረዋል። በተለይም "በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት የኑሮ እጥረት ያጠቃቸውን ወገኖች ካለን ከፍለን በመመገብና በማልበስ ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነት ማረጋገጥ ይገባል" ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ተከታዮች ጥሪ አቅርበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም