ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ግመል ከነ ግልገሏ ተሸለሙ

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 29/2011 የሱማሌ ክልል ለኦሮሚያ ክልል ምክትል አቶ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ግመል ከነ ግልገሏ ሸልሟቸዋል። ትናንት በጅግጅጋ የተጀመረው የኦሮሞና ሱማሌ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የውይይት መድረክ ዛሬም በጀረር ዞን ደገ ሀቡር ከተማ ቀጥሏል። በኦሮሚያ ክልል ምክትል አቶ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ልዑክ ከሱማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሐመድ ጋር ደገ ሀቡር ሲገቡ የከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በመድረኩም ለምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ ግመል ከነ ግልገሏ ተበርክቶላቸዋል፤ ግመል እንዴት ማጥባት(ማለብ)  እንደሚቻልም ትምህርት ተሰጥቷቸዋል። ጎን ለጎንም ሁለቱ ምክትል ፕሬዝዳንቶች በደገ ሀቡር ችግኝ ተክለዋል። አቶ ሽመልስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ብዙ ትግል በተደረገባትና ታጋይ ህዝብ ባለባት ደገ ሀቡር በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ከተማዋን ተመሳሳይ ህዝባዊ ትግል ከሚደረግባቸው የኦሮሚያ ከተሞች ጋር እናስተሳስራለንም ብለዋል። "ነፃነት ሂደት ነው" ያሉት አቶ ሽመልስ፤  "የተገኘው ነፃነት ስር እንዲሰድም በትውልድ ቅብብሎሽ መስራት ይጠበቃል" ሲሉም ተናግረዋል። ሁለቱ ህዝቦች በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በባህልና በማህበራዊ አኗኗር ተመሳሳይና አንድ ህዝብ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ። ጥራት ያለው ትምህርት ላይ በመትጋት በፌዴራል ደረጃ እኩል ውክልና እንዲኖር መታገል አለብን ሲሉም ተናግረዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከወንድም ህዝብ ከኦሮሞ  ጋር በመሆን በጋራ አገር ለመገንባት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል። በአዳማ በነበረው የሁለቱ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ፈረስ ከጦርና ጋሻ ጋር እንደተበረከተላቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም