በሐረሪ ክልል የጤና ባለሙያ እጥረት ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል... የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የጤና ባለሙያ እጥረት ለመፍታት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል... የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር
ሐረር (ኢዜአ) ሐምሌ 28 ቀን 2011- በሐረሪ ክልል በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት ችግር ለመፍታት እየተከናወነ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ። ሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በስምንት የጤና ትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪና በደረጃ አራትና አምስት ያሰለጠናቸውን 846 ተማሪዎች ትናንት አስመርቋል። ኮሌጁ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ባለ 3 ፎቅ ሁለገብ ዘመናዊ የመማሪያ ህንጻም ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ እንዳሉት የክልሉ መንግስት ብቃት ያላቸው፣ በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑና ኃላፊነት የሚሰማቸው ወጣትና ተተኪ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የጀመራቸውን ስራዎች ለማጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። ታዳጊ ክልሎች በጤናው ዘርፍ የባለሙያ እጥረት እንዳያጋጥማቸው ኮሌጁ እያከናወነ የሚገኘውን የሰው ኃይል የማፍራት ሥራ በቀጣይም ሊያጠናክር እንደሚገባ የገለጹት አቶ ኦርዲን፣ ተመራቂ ተማሪዎች ሙያው በሚፈቅደው ስነምግባር መሰረት ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል። የኮሌጁ ዲን አቶ ያሲን አብዱላሂ በበኩላቸው የዕለቱ ምሩቃን በመጀመርያ ዲግሪ፣ በደረጃ አራት እና አምስት የትምህርት መርሃግብሮች የንድፈሀሳብና የተግባር ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዕለቱ ተመራቂዎቹ መካከል 511ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተመልክቷል። እንደአቶ ያሲን ገለጻ ተመራቂዎቹ ከኦሮሚያ፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር፣ ከሐረሪ፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡ ናቸው። “ይህም ኮሌጁ በተለይ በታዳጊ ክልሎች በጤናው ዘርፍ የሚታየውን የባለሙያ እጥረት ችግር ለመፍታት እየሰራ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ከዕለቱ ምሩቃን መካከል የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ሳሮን አለማየው በቀጣይ በትምህርት ቆይታዋ ያገኘችውን ዕውቀት ተጠቅማ ያስተማራትን ህብረተሰብ ለማገልግል ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች። “በመንግስት በኩል የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ የተጣለብኝን አገራዊ አደራ እወጣለው” ያለችው ሌላዋ የማዕረግ ተመራቂ ደግሞ ጺዮን ጸጋዬ ናት። የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ2011 የትምህርት ዘመን 3ሺህ 487 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ አቶ ያሲን ጠቁመዋል። ኮሌጁ ከተመሰረተ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ከ10ሺህ የሚበልጡ የጤና ባለሙያዎችን በሰርተፍኬት፣ በዲፕሎማና በመጀመሪያ ዲግሪ አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።