የቴክኖሎጂ ጎርፍ ሰለባ ከመሆን በቴክኖሎጂ አገርን ለመገንባት ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል-ወይዘሮ ቤተሊሔም አበራ

72
ሐምሌ 28/2011 የቴክኖሎጂ ጎርፍ ሰለባ ከመሆን በቴክኖሎጂ አገርን ለመገንባትና ችግርን ለማስወገድ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ የቀማሪዋ እንስት ድርጅት መስራችና ስራስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሔም አበራ ተናገሩ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከ'U Code Girl'/ቀማሪዋ እንስት/ ድርጅት ጋር በመተባበር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ችግርን መፍታት በሚል መርህ ለሴቶች ተማሪዎች የኮምፒዩተር ስልጠና ሰጥተዋል። ለአምስት ቀናት በቆየው በዚህ ስልጠና ከ20 በላይ ከሚሆኑ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 130 ሴት ተማሪዎች ተሳትፈዋል። የ'U Code Girl'/ቀማሪዋ እንስት/ ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሔም አበራ በስልጠናው ማጠቃለያ እንዳሉት በዚህ ቴክኖሎጂ ግዴታ በሆነበት ዘመን የቴክኖሎጂ ጎርፍ ሰለባ ከመሆን ይልቅ በቴክኖሎጂ አገርን መገንባትና ችግረን ማቅለል ማስቻል የስልጠናው ዓላማ ነው። ስራ አስኪያጇ አክለውም ቴክኖሎጂን አውቀን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለበጎ ዓላማ ማዋል እንደሚቻልም ተናግረዋል። አያይዘውም የኮምፒዩተር ትምህርት ከንድፈ ሐሳብ ይልቅ በተግባር የታገዘ እንዲሆንና ሴቶች ለሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ የትምህርት ዘርፍ ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግም ሌላው ዓላማው ነው። በስልጠናው የተካፈሉት ሴቶች ተማሪዎችም ቴክኖሎጂን በመታገዝ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን ማቅለል እንደሚቻል በተግባር ያሳያቸው ትምህርት ማግኘታቸውን አወስተው የራሳቸውንም ሶፍትዌር ተጠቅመው ችግር ፈች ፈጠራዎችን ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሰልጣኞቹ በስልጠናው ቴክኖሎጂን በመታገዝ ሊፈቱ ይችላሉ የሚሏቸውን ችግሮች እንደለዩና በዚያ ላይ ስልጠናው እንደተሰጣቸውም አክለዋል። በስልጠናው የላቀ እንቅስቃሴ ለነበራቸው ተማሪዎች የኮምፒዩተር ሽልማት ተበርክተውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም