ቀጥታ፡

ምሩቃን ለሀገራዊ ለውጡ እውን መሆን ተግተው እንዲሰሩ ተጠየቀ

ጋምቤላ (ኢዜአ) ሐምሌ 28 ቀን 2011- ተመራቂ ተማሪዎች አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን በማጠናከር ሀገራዊ ለውጡ እውን እንዲሆን ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 790 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ምሩቃን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያካበቱትን የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ በማጠናከር ሀገራዊ ለውጡን እውን ለማድረግ ተግተው ሊሰሩ ይገባል፡፡ በቀጣይ ሥራ ፈላጊ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ በመሆን ለአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡ “ተመራቂዎች በትምህርት የገበዩትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ ሥራዎችን ማከናወን አለባቸው” ያሉት ፕሮፌሰር አፈወርቅ፣ በአገሪቱ የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ሥራ እውን እንዲሆን ትኩረት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው ተመራቂዎች ከአካባቢያዊ አስተሳሰብና ከአድልኦ አሰራር በመወጣት ለአገሪቱ ሰላምና ልማት ጠንክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ሂደቱን በማስፈን ተማሪዎች የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲመለሱ ላደረገው ጥረት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዩኒቨርሲቲው ስኬታማነት የክልሉ መንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ ለተነደፈው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ ናቸው። ተቋሙ በዛሬው እለት በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በቀንና በማታው በተለያዩ የትምሀርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 790 ተማሪዎች ማስመረቁን ተናግረዋል፡፡ ከተመራቂዎች መካከል 742ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው ከግሪን የምርምርና ልማት ተቋም ጋር በመተባበር በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም